የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት በተከናወነው የታላቁ ሩጫ ፕሮግራም ማስተዋወቂያ ላይ በመገኘት ለታዳጊ ተማሪዎች ስለምርጫ ምንነትና የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተግባር የተደገፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ አደረገ፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች ሩጫ አስተባባሪዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለመነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ፕሮግራሙን አስተዋውቋል፡፡ በዚህ መርሀ ግብር ላይ የተጋበዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በተለይም ለታዳጊ ተማሪዎች ስለምርጫ ምንነት እና በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ዙሪያ በተግባር የተደገፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ አድርጓል፡፡
ከስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት እና ከስርዓተ-ጾታና አካታችነት ሥራ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በቦታው የተገኙ ሲሆን ዜጎች በምርጫ ተሳትፎ ውስጥ ምን ማሟላት እንዳለባቸውና ድምጻቸውን ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ እንዴት መስጠት እንዳለባቸው ለታዳጊ ተማሪዎቹ ተግባራዊ ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ታዳጊ ተማሪዎቹ የድምጽ አሰጣጥን በተመለከተ ተግባራዊ ልምምድ ያደረጉ ሲሆን ለዚሁ ጉዳይ የተዘጋጀ ሚስጥራዊ ድምጽ ለመስጠት የሚረዳ መከለያ፣ የመለማመጃ የድምጽ መስጫ ወረቀትና የድምጽ መስጫ ሳጥን በመጠቀም የናሙና ምርጫና የድምጽ አሰጣጥ ሂደት አከናውነዋል፡፡
ይህን መሰሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ታዳጊዎች በምርጫ ብቻ ስለሚደረግ የስልጣን ሽግግርና የምርጫ ሂደት በቂ መረጃ እንዲኖራቸው እና ከወዲሁ በምርጫ ስለመሳተፍ ጠቃሚነት ተረድተው ዝግጅት እንዲያደርጉ ለማገዝ ያለመ ነው፡፡