የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የሕትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት በትምህርት ተቋማት፣በህዝብ ቤተ- መጻሕፍት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ በማስቀመጥ ለዜጎች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መሀከል መራጮች በቂ የምርጫ ነክ ግንዛቤ የሚያገኙበትን ስልት መቀየስና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርትን መስጠት አንዱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርትን በቋሚነት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የሕትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት በትምህርት ተቋማት፣በህዝብ ቤተ- መጻሕፍት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ በማስቀመጥ ለዜጎች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።
ይህንንም ተከትሎ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ ምን አይነት የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች፣ ምርጫ በኢትዮጵያ፣ ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ፣ ዲሞክራሲ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ እንዲሁም የምርጫ ሂደት በሚል ርዕስ የተዘጋጁ 1000 ብሮሸሮችን፤ ወደ 150 የሚደርሱ በኪስ መያዝ የሚችሉ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በብሬል ጭምር የተዘጋጁ አዋጆችን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አስረክቧል፡፡
በተጨማሪም የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ክፍል ከቦርዱ ዶክመንቴሽን ክፍል ጋር በመተባበር በቦርዱ ቤተ-መጻሕፍት የሚገኙ በጥንታዊ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ሕግ፤እና ፍልስፍና ዙሪያ የተፃፉ እና ለተመራማሪዎች ጠቃሚ እንደሆኑ የታመኑ የሕትመት ዉጤቶችን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ገቢ አድርጓል፡፡
በዚሁ አጋጣሚም ቦርዱ ወደፊትም የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርትን በቋሚነት ተደራሽ ለማድረግ የሚጠቅሙ የተለያዩ የሕትመት ውጤቶችን እንዲሁም የምርምር እና የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚረዱ ተጨማሪ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት እና ለሌሎች የንባብ ማዕከላት ለማጋራት ያለውን ዕቅድ ለማሳወቅ ይወዳል፡፡
የታህሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም.
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ