የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በዎላይታ ዞን የሚያስፈጽመው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ምርጫ የድምፅ መስጠት ቀንን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ቦርዱ በዎላይታ ዞን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ. ም. የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ ድምፅ የመስጠት ሂደትን እንደሚያስፈጽም ይታወቃል። በዚህም መሠረት በዕለቱ የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ ድምፃቸውን መስጠት እንዲችሉ እንዲሁም የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ለማስቻል፤ ቦርዱ የሚከተሉት ተግባራት ተፈጻሚ እንዲሆኑ የምርጫ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የሥነ‐ምግባር ዐዋጅ 1162/ 2011 አንቀጽ 161 የመተባበር ግዴታ መሠረት ለመንግሥታዊና ለማንኛውም መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ያሳውቃል። በመሆኑም

• ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ በዞኑ የሚገኙ የፌዴራልና የክልል መንግሥታዊ ተቋማት ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ. ም. ሥራ ዝግ እንዲያደርጉ፣

• ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጠት ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ በዞኑ የሚገኙ ማንኛውም መንግሥታዊ ያልሆኑና የግል ተቋማት በተመሳሳይ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ. ም. ዝግ እንዲያደርጉ፣

• የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ማለትም ሆስፒታሎችን ጨምሮ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት …ወ. ዘ. ተ) በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ ማከናወን የሚችሉ ሲሆን፤ የመተባበር ግዴታው እነዚህን ተቋማት እንቅስቃሴ መዘጋት አያስገድድም።

• የትራንስፓርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢሆንም በዞኑ ዜጎች ድምፅ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ሁነቶችንና ዕቅዶችን እንዳይይዙ እንዲሁም እንቅስቃሴያቸውን ድምፅ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ ያበረታታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኔ 10 ቀን 2015 ዓ.ም.