Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን በሚካሄደው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ምርጫ የመራጮች ትምህርት ላይ ከሚሣተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን በሚካሄደው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔን ምርጫ ላይ የመራጮች ትምህርት ተደራሽነት ላይ ለሚሠሩና በቦርዱ የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገላቸው ሰባት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አካሄደ። ዐላማውን ድጋፍ የሚደረግላቸው ድርጅቶች የሚደረግላቸውን ድጋፍ በምን አግባብ መጠቀም እንዳለባቸው፤ እንዲሁም ከዕቅድ አንጻር አፈጻጸማቸውና የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረባቸውን አስመልክቶ ግልጽ መግባባት ላይ ለመድረስ ያደረገውን ውይይት በንግግር የከፈቱት የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር አበራ ደገፋ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ ካስፈፀመባቸው አካባቢዎች የወላይታ ዞን አንዱ እንደሆነ አስታውሰው፤ በዞኑ ላይ በተካሄደው የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ ሂደት ላይ ጉልህ የሕግ ጥሠት መፈጸሙን ተከትሎ ውጤቱ እንደተሠረዘና አሁንም ቢሆን የድጋሜ ሕዝበ ውሣኔ ሂደቱ ላይ ተመሳሳይ የሕግ ጥሠት ቢፈጸም፤ የቦርዱ ውሣኔ ከቀደመው የተለየ እንደማይሆን፤ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህ እንዳይሆን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ አሳስበዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ዋና ዓላማ የመራጮች ትምህርቱን የተደራሽነት ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ማድረስ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ድርጅቶቹም ይሄንኑ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ፤ የሥራ ሪፖርትም ሲያቀርቡ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በምን መልኩና በምን ያህል ተደራሽ እንዳደረጉ በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅባቸው፤ ቦርዱም ለዚህም የሚሆን የሪፖርት ማድረጊያ ቅጽ አዘጋጅቶ እንደሚልክ ተገልጿል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ በዕቅዳቸው መሠረትና የተደረገላቸውን የገንዘብ ድጋፍ በመጠቀም እያንዳንዳቸው የት እና በምን መልኩ የመራጮች ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ እንዳሰቡ የገለጹ ሲሆን፤ ገለጻቸውንም ተከትሎም የድርጅቶቹ ዕቅድ ግልጽና የሚለካ መሆን እንዳለበት፤ ይህም ሲባል የመራጮች ትምህርት ለማስተማር በዕቅድ በያዟቸው ወረዳዎች ውስጥ ያሉትን ልዩ ሥፍራዎችና ተደራሽ የሚደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በጊዜ መለየት እንዳለባቸው አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የመራጮች ትምህርቱ በሚሰጥበት ወቅት በዞኑ የተካሄደው ሕዝበ ውሣኔ እንዲደገም ያደረጉት ምክንያቶችን በማስታወስ የሕግ ጥሠቶቹ እንዳይደገሙ ዜጎች የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ እንዲሁም መራጮች የመራጮች ምዝገባውና ድምፅ የመስጠት ሂደቱ በተመሳሳይ ቀን የሚደረግ መሆኑን ተረድተው በዕለቱ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት መረጃዎቻቸውን በአግባቡ በማስሞላትና በመፈርም ድምፃቸውን መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸው ተገልጿል።

በውይይቱ መጨረሻም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ በተሰጠው አስተያየት መሠረት ሁሉንም የዞኑ ወረዳዎች በመራጮች ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል፤ በዞኑ ቀድሞ በነበሩት ሰባት ወረዳዎች ወይም በአዲሱ አወቃቀር ባሉት 18 ወረዳዎች እና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች ተከፋፍለው ትምህርቱን ለመስጠት ተስማምተው የውይይቱ ማብቂያ ሆኗል።

Share this post