Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የሚካሄደውን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔን ምርጫ በተመለከተ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር ምክክር አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የሚደረገውን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ምርጫ አስመልክቶ በመራጮች ትምህርትና በምርጫ መታዘብ ላይ ከተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ክትትል ተግባራት ላይ ከተሠማራው ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር ሚያዚያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አካሄደ። የውይይት መድረኩ የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ባደረጉት ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የድጋሚ ምርጫ ማካሄድ ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች አብራርተዋል። በተጨማሪም የመራጮች ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት ምን ምን ጉዳዮች መካተት እንዳለባቸው እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ተደራሽ ሊደረጉ የሚችሉበትን አግባብነትና አማራጮች አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተጨማሪ 12 ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን፤ ከምርጫ ቦርዱም የመራጮች ትምህርት ክፍል፣ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል፤ የውጭ ግንኙነት ሥራ ክፍል እና የሥርኣተ-ፆታና አካተችነት ሥራ ክፍል ኃላፊዎች ተሣትፈዋል። በውይይቱም የድጋሚ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳን፣ የድጋሚ ምርጫ ዕቅድና ማሻሻያዎችን፣ የሥርአተ ፆታና አካታችነት ጉዳዮችን፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኩል የተሣትፎ ዕቅድና የታሰቡ ተግባራትን፣ የዕውቅና መታወቂያ አሰጣጥና ሂደትን፣ እንዲሁም ባለፈው ሕዝብ ውሣኔ በምርጫ መታዘብና በመራጮች ትምህርት እንቅስቃሴዎች ሂደት የተገኙ ትምህርቶች እና ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት ተደርገውባቸዋል።

ለተሣታፊዎቹም ቀደም ሲል በወላይታ ዞን ላይ በተካሄደው ሕዝበ ውሣኔ የመራጮች ምዝገባና በምርጫው ቀን ያጋጠሙ የሕግ ጥሠቶችን በተመለከተ ቦርዱ ባረደገው የክትትልና የማጣራት ሥራ ከፍተኛ የሕግ ጥሠት መኖሩን በማመን ጉዳዩ በፌደራለ ፖሊስ ማጣራት እንዲደረግበት ያደረገ መሆኑንና በዚህም እስካሁን ድረስ በፌደራል ፖሊስና በፍትሕ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራ የክትትል ሥራ ውጤትን አስመልክቶ ገለጻ ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የፋይናንስ ድጋፍ ዕጠረት፣ የጊዜ ሁኔታ እና የሰው ኃይል ዕጥረት ተሣታፊዎቹ እንደተግዳሮት ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ከዚህ በፊት የተከሰቱ ችግሮች እንዳይደገሙ የመራጮች ትምህርት፤ የመታዘብ እና የሰብኣዊ መብት ክትትል ሥራዎችን በላቀ ትጋት፣ ዝግጅትና ጥንቃቄ ሊተገበሩ እንደሚገባ፤ ቦርዱም ይህ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ መረጃ የሚያጋራ መሆኑ ተገልጿል። በውይይቱ ማጠቃለያም ሁሉም ተሣታፊዎች የየበኩላቸውን ኃላፊነት በመወጣት የድጋሚ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

Share this post