Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሣኔውን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ማድረግ ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአሌ፣ በአማሮ፣ በዲራሼ) ላይ ያካሄደው የሕዝበ ውሣኔ ድምፅ የመስጠት ሂደት መጠናቀቁን ተከትሎ፤ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ውጤት የማዳመር ሥራው ድምፅ በተሰጠባቸው ጣቢያዎች የተከናወነ ሲሆን፤ ውጤቱም ጥር 30 ቀን 2015 ከጠዋት ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎች ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል።

የተዳመረና የተመሳከረ ጊዜያዊ ውጤት በልዩ ወረዳ ደረጃ ይፋ ከተደረገባቸው ውስጥ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ እና ባስኬቶ ሲጠቀሱ፤ በዞን ደረጃ ደ’ሞ በኮንሶ ይፋ ተደርጓል። በተጠቀሱት ቦታዎች የጊዜያዊ ውጤቱ የማዳመርና ማመሳከር ሥራው ከጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የተሠራ ነው።

ከላይ በተጠቀሱት ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የምርጫ ቁሳቁሶችና የምርጫ ውጤቶች ወደ ማዕከላት የተሰበሰበ ሲሆን፤ በቡርጂ ልዩ ወረዳም እንዲሁ ውጤት የማዳመር ሥራው በመሥራት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፤ በጌዲኦ እና በጎፋ ዞኖች በማስተባበሪያ ማዕከል ደረጃ የማመሳከር ሥራ ተጠናቆ በዞን ደረጃ ለሕዝበ ውሣኔ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች በማስረከብ ላይ ይገኛሉ። በቀጣይም በነዚህ ዞኖች የውጤት ማዳመርና ማመሳከር ሥራው እንደተጠናቀቀ ጊዜያዊ ውጤቶቹ ለሕዝብ ይፋ የሚደረጉ ይሆናል።

ከሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተሰበሰበውን ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሚያከናወን ሲሆን፤ ይህም በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የሚደረገው የመጨረሻ ውጤት የማረጋገጥ ሥራ ሲጠናቀቅ በቦርዱ ፀድቆ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል።

ቦርዱ በድምፅ መስጫው ቀን በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በመከናወን ላይ የነበረውን ድምፅ የመስጠት ሂደት የጎበኘ ሲሆን፤ በማዕከል ደረጃም በወላይታና በጨንቻ የተካሄደውን የውጤት ማዳመር ሥራ ጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Share this post