Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ዲራሼ) ላይ እያካሄደ ባለው የሕዝበ ውሣኔ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው መራጮች ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ እያካሄደ ባለው የሕዝበ ውሣኔ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው መራጮች ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ

ቦርዱ በተለያዩ የመርጫ ጣቢያዎች ላይ እያደረገ ባለው ክትትል መሰረት የደረሰባቸው ግኝቶች እና የወሰዳቸው እርምጃዎች ከስር ተዘርዝረዋል

• 9 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተለያዩ የምርጫ ቁሳቁስ ጉድለት ሪፓርት የተደረገ ሲሆን ይህንኑ ለመቅረፍ በምርጫ ማእከል ደረጃ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል

• 38 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለድምፅ መስጫ ቀን ከተመደቡ ተጨማሪ አስፈፃሚዎች ውስጥ በድምፅ መስጫ ቀን በጣቢያዉ ያልተገኙ በመኖራቸው ቦርዱ ይህንኑ ለማስተካከል ጥረት እያደረገ ይገኛል

• የድምፅ መስጫ ወረቀት ጉድለት በተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ 11 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተከስቶ የነበረ ሲሆን ይህንኑ ለመቅረፍ ከዞንና ከወረዳ ማስተባበሪያ ማእከላት በመጠባበቂያ ከተያዘው ላይ እንዲሟላ ተደርጓል

ህግ መተላለፍን በተመለከተ

• ቦርዱ ከሰዓታት በፊት ይፋ ያደረገውን የወላይታ ዞን ሶርቶ ቀበሌ ሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ ላይ የተፈፀመ የሕግ ጥሠትን ተከትሎ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ፓሊስ ኮሚሽን በደብዳቤ ቁጥር 2ህ/6851/71/1 በላከው መረጃ በምርጫ ጣቢያው ላይ ተፈጸመ የተባለው የሕግ ጥሠት ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ለቦርዱ አሳውቋል። በዚህም መሠረት የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ መስቀሌ ባሳን እና አቶ አበበ አይዛ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በፓሊስ ኮሚሽኑ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ተገልጿል። በመሆኑም ቦርዱ በሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ የተቋረጠውን የድምፅ የመስጠት ሂደት እንዲቀጥል ወሥኗል።

• በይርጋ ጨፌ ማስተባበሪያ ማእከል ስር በሚገኘው አዳሜ ምርጫ ጣቢያ ሱኬ ላይ የምርጫ ጣቢያው ሠራተኛ ወደ መራጮች የሚሥጥር ድምፅ መስጫ/መከለያ በመግባትና መራጮች ድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ ምልክት ሲያደርጉ በማየቱ እንዲሁም በተመሳሳይ ጣቢያ ሌላ የጣቢያ ሰራተኛ የድምጽ መስጫ ወረቀትን መራጮች ወደ ሳጥን ከማስገባታቸው በፊት ተቀብላ ከፍታ ስታይ የተገኘች በመሆኑ በዐዋጁ የተደነገገውን የመራጮች በሚሥጥር ድምፅ የመስጠት መብትን ተላልፈው በመገኘታቸው በተፈፀመው የሕግ ጥሠት ላይ ቦርዱ በጣቢያው ሠራተኞችን ከስራ የማሰናበት ዕርምጃ ወስዷል። በቀጣም ይህን ጣቢያ አስመልቶ ሌሎች እምጃዎች ሲኖሩ ቦርዱ የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡

• በጋሞ ሰላም በር በዶሞኦ ቀበሌ በዶሞኦ ምርጫ ጣቢያ ወማለ 1 ላይ 17 መራጮች ከቀበሌ ደብዳቤ በማጻፍ ያለምንም የማንነት ማረጋገጫ ሊመርጡ የነበረ በመሆኑ እንዲሁም ከተመዘገቡበት ማንነት ጋር ያልተገናኘ የመታወቂያ ወረቀት እና የድምጽ መስጫ ካርድ ይዘው ወደ’ምርጫ ጣቢያ ለመምረጥ የመጡ ግለሰቦች ድምጽ እንዳይሰጡ ተደርጓል።

Share this post