Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ አስመልክቶ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የሕዝበ ውሣኔው ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለሚያሠለጥኑ ባለሞያዎች ሥልጠና መሰጠት ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የውጤት ማመሳከር፣ የማዳመርና ይፋ የማድረግ ሂደትን አስመልክቶ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የሕዝበ ውሣኔው ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለሚያሠለጥኑ ባለሞያዎች ሥልጠና መሰጠት ጀመረ። በዚህ መሠረት እስካሁን የሚከተሉት ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፦

- በሕዝበ ውሣኔ የድምፅ መስጫ ቀን የውጤት ማመሳከርና የማዳመር ሥልጠና ለመሪ አሠልጣኞች እና ለተወሠኑ የቦርዱ ኦፕሬሽን ክፍል ባልደረባዎች ጥር 4 እና ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሁም ጥር 8 እና ጥር 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተሰጥቷል።

- በሕዝበ ውሣኔው ድምፅ መስጫ ቀን፤ የውጤት ማመሳከር ሂደት ላይ ከ26 የማስተባበሪያ ማዕከላት ለተውጣጡ 121 አስፈጻሚዎች ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የአንድ ቀን ሥልጠና በአርባ ምንጭ ከተማ ተሰጥቷል።

- በሕዝበ ውሣኔ ድምፅ መስጫ ቀን፤ በውጤት ማዳመር ሂደት ላይ ከዞን እና ከልዩ ወረዳዎች የሕዝበ ውሣኔው ማስተባባሪያ ጽ/ቤት እንዲሁም ከተመረጡ የማስተባበሪያ ማዕከሎች ለተውጣጡ 51 አስፈጻሚዎች ጥር 14 እና ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የሁለት ቀን ሥልጠና በአርባ ምንጭ ከተማ ተሰጥቷል።

- በሕዝበ ውሣኔ ድምፅ መስጫ ቀን፣ ድምፅ ቆጠራ እና ውጤት በጣቢያ ደረጃ ይፋ የማድረግ ሂደት የተመለከተ ሥልጠና ለ250 የመሥክ አሠልጣኞች “የአሠልጣኞች ሥልጠና” የሚሰጥ ሲሆን፤ ለ135 የመሥክ አሠልጣኖች በመጀመሪያ ዙር ጥር 14 እና ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቷል። የሁለተኛው ዙር የአሠልጣኞች ሥልጠና ለ117 ሠልጣኖች ጥር 17 እና 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚሰጥ ይሆናል።

- የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች የምርጫ ቀን ሥልጠና ከጥር 19 እስከ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በሦስት ዙር በ31 ማዕከሎች የሚሰጥ ይሆናል።

Share this post