የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ማለትም በጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዲዮ እና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ላይ የሚካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ መሰረት የመራጮች የግል ውሳኔ በመረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያስችል በቂ መረጃ እና ሀሳብ እንዲያገኙ ለማድረግ ቦርዱ በህዝበ ውሳኔው አማራጮች ላይ ሃሳቦች እና አስተያየቶች ወደ ህዝብ የሚቀርብባቸውን የክርክር፣ የውይይት፣ እና የምከክር መድረኮችን በማመቻቸት ላይ ይገኛል።
ስለሆነም በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ የምትፈልጉ የሲቪልማህበራት፣ ህዝበ ውሳኔው በሚካሄድባቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የምትንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ መሳተፍ የምትፈልጉ በቂ ተያያዥ የትምህርት እና የስራ ልምድ ብቃት ያላችሁ ግለሰቦች እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የፍላጎት መግለጫ ወረቀት በኢሜል አድራሻችን media [at] nebe.org.et በመላክ ወይም ፍላሚንጎ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ጽህፈት ቤት 1ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 106 በግንባር በመቅረብ እንድታስገቡ ቦርዱ ጥሪ እያቀረበ የፍላጎት መግለጫ ሰነዱ የሚመለከቱትን ነጥቦች (እንደ የአግባብነቱ) ሊያሟላ እንደሚገባ ያሳውቃል።
1. ሲቪል ማህበራት
- በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የምታቀርቡትን ሃሳብ አጭር ማብራሪያ፤
- የውይይት ሂደቱ ሃሳብ ተደራሽ የሚያደርገውን የህብረተሰብ ክፍል (target audience) ዝርዝር፤
- ውይይቱን ለማከናወን የሚጠቀሙበትን ቋንቋ(ዎች)፤ እንዲሁም
- ስልጣን ከተሰጠው አካል የተሰጣችሁን የማህበራት ምዝገባ ሰነድ ።
2. የፖለቲካ ፓርቲዎች
- በሕዝበ ውሣኔው ላይ ያላቸው አቋም (ድጋፍ ወይም ተቃውሞ) አጭር ማብራሪያ ከነመነሻ ምክንያቱ፤
- ክርክሩን ለማከናወን የሚጠቀሙበትን ቋንቋ(ዎች)፤ እንዲሁም
- የክርክር ሂደቱ ሃሳቡ ተደራሽ እንዲሆንላቸው የሚፈልገውን የህብረተሰብ ክፍል (target audience)፤
3. ግለሰቦች
- በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የምታቀርቡትን ሃሳብ
- በጉዳዩ ላይ የትምህርት እና የስራ ልምድ ዝግጅቱ ያላቸው የሚገልፅ ሲቪ፤ እንዲሁም
- ከህዝበ ውሳኔ ጥያቄው ጋር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የተያየዘ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስተማሩ ወይም ፣ ግለሰቦችና ባለሙያዎች ብቃታቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ (ምሳሌ፦ ያሳተሙዋቸውን ፅሁፎች)፤
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ