የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ላይ ያሳለፈውን የመሠረዝ ውሣኔ አነሣ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ጉሕዴን) በዐዋጅ 1162/2011 እና ይህንኑ ዐዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ቦርዱ ባወጣው መመሪያ ቁጥር ሦስት መሠረት በዳግም ምዝገባ ሂደት ውስጥ ማለፍ ከነበረባቸው ፓርቲዎች መካከል አንዱ ስለነበር፤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ መተዳደሪያ ደንቡን አሻሽሎ እንዲያቀርብ በወቅቱ መመሪያ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና ፓርቲው ለዳግም ምዝገባ የሚያበቃውን ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታ በወቅቱ ባለማሟላቱ ከምዝገባ እንዲሠረዝ ቦርዱ ወሠነ፡፡
ፓርቲው የዳግም ምዝገባ ሂደቱ በሚከናወንበት ወቅት የፓርቲው አመራሮቹ በሙሉ እንዲሁም አባላቱ በእሥር ላይ መሆናቸውን ገልጾ ቦርዱ በፓርቲው ላይ የሰጠውን ውሣኔ እንዲያነሣ አቤቱታ አቀረበ፤ ቦርዱም ፓርቲው ያቀረበውን አቤቱታ ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በመመርመር ፓርቲው በወቅቱ የተጠየቀውን ያላሟላው ከዐቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ገጥሞት መሆኑን ተገንዝቦ የመሠረዝ ውሣኔውን አንሥቷል፡፡ የውሣኔውን ዝርዝር ከተያያዘው ደብዳቤ እዚህ ላይ ያገኙታል፡፡