Skip to main content

በደ/ብ/ብ/ህዝቦች ክልል 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔ ዙሪያ የመራጮች ትምህርት መሰጠት ለሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የቀረበ ጥሪ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኙ 6 ዞኖች ማለትም የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች ማለትም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔ ያካሂዳል ፡፡

ዜጎች ህዝበ ውሳኔው ላይ ያላቸውን ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማረጋጋጥ ብሎም ተአማኒነትን ያተረፈ ሰላማዊ ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ የመራጮች ትምህርት አስፈላጊነት እሙን ነው፡፡ ይህንን አላማ ለማሳካትም የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎ ትልቅ ስፍራ ይይዛል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቦርዱን ባቋቋመው አዋጅ ቁጥር 1133/2011 እንዲሁም የመራጮች ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ እና የሥነ ምግባር መመሪያ ቁጥር 04/2012 መሰረት በህዝበ ውሳኔው ሂደት የመራጮች ትምህርት መስጠት ለሚፈልጉ እና ትምህርቱን ለመስጠት ብቃት ላላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ሠጥቶ ማሰማራት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡

በዚህ መሠረት፡-

  • በህግ ተመዝግባችሁ የምትንቀሳቀሱ፤
  • የማስተማሩን ተግባር ለመወጣት የሚያስችል ብቃት ያላችሁ፤
  • ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ የሆናችሁ፤
  • በተለያየ ዘዴ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት የምትፈልጉ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከስር በሚገኘው ማስፈንጠሪያ የሚገኘውን ማመልከቻ በመሙላት አግባብነት ካለቸው ሰነዶች (ማለትም የምዝገባ ሰርተፊኬት ቅጂ፣ ለአሰተባባሪዎችና አሰልጣኞች አባሪ ቅጽ፣ የስልጠና እቅድ እና ለስራ የሚያስፈልግ በጀት…) ጋር በማያያዝ በኢሜል አድራሻ votersedu [at] nebe.org.et እንድትልኩ ወይም በዋናው መ/ቤት ቢሮ ቁጥር 102/106 ወይም ለቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ጥቅምት 16 ቀን ጀምሮ በ10 ቀናት ውስጥ በኣካል እንድታቀርቡ ቦርዱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አመልካቾች የማመልከቻውን ፎርም እና አያይዘው የሚያቀርቡአቸውን ሰነዶች ዝርዝር፣ ከስር ከሚገኙ ማስፈንጠሪያዎች ወይም ከዋናው መሥሪያ ቤት እና ከክልል ጽህፈት ቤቶች ማግኘት እንደሚቻል እየገለጽን ከዚህ በፊት የማስተማር ፈቃድ ጥያቄ ያቀረባችሁ ማህበራትም ለእናንተ በተለይ የተዘጋጀውን ማመልከቻ ሞልታችሁ ልታቀርቡ እንደሚገባ እናሳውቃለን፡፡ ከዚህ በፊት ለስድስተኛው አገር ዓቀፍ ምርጫ የመራጮች ትምህርት ፈቃድ የወሰዳችሁ ተቋማትና አዳዲስ አመልካቾች የቀረቡላችሁ ቅጾች የተለያዩ መሆኑን አስተውላችሁ እንድትሞሉ እናሳስባለን፡፡

ለአዲስ አመልካቾች የመራጮች ትምህርት የመስጠት ፈቃድ ለማግኘት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚቀርብ ማመልከቻ ቅጽ

የመራጮች ትምህርት የመስጠት ፈቃድ ለማሳደስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚቀርብ ማመልከቻ ቅጽ

አባሪ ቅጽ ለአሰተባባሪና አሰልጣኝ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም

Share this post