ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ) በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ ቦርዱ ውሣኔ ሰጥቷል
ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዉ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ) መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን የቦርዱ ታዛቢ በተገኙበት አካሂዷል፡፡ ቦርዱም የፓርቲውን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ሪፖርትና የታዛቢውን ሪፖርት ከሕጉና ከመተዳደሪያ ደንቡ አንፃር መርምሯል፡፡
ፓርቲው በዚሁ ጉባኤው የማእከላዊ ምክር ቤት አባላት፤ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት እና የፓርቲው ፕሬዚዳንት ምርጫ እጅ በማውጣት ያከናወነ መሆኑን ከፓርቲው እና ከታዛቢው ሪፖርት ቦርዱ ተገንዝቧል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 74 (3) የፓርቲ አመራሮች እና በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች አመራረጥ ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ መከናወን ያለበት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ፓርቲው በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ኃላፊዎችን የመረጠበት አካሄድ የአዋጁን አስገዳጅ ድንጋጌ የተቃረነ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በሌላ በኩልም ፓርቲው በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተሻሽለው ሊካተቱ የሚገባቸውን አንቀፆች አስተካክሎ ያላቀረበ መሆኑንም ቦርዱ ተረድቷል፡፡
በመሆኑም ፓርቲው ይህ ውሣኔ ከተገለፀለት ከጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በ4ወራት ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ በማድረግ፤ የማዕከላዊ ምክር ቤት፣ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትንና የፕሬዚዳንቲዊውን ምርጫ ግልፅ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና በሚስጥር በሚሰጥ ድምፅ እንዲያስመርጥ፤ በተጨማሪም በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተሻሽለው ሊካተቱ የሚገባቸውን አንቀፆች ላይ ተገቢውን ማስተካከያ በማድረግ በጠቅላላ ጉባኤ አፀድቆ እንዲያቀርብም ቦርዱ ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በአካሄደው ስብሰባ ወስኗል፡፡