የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸምን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸምን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ያካሄደው ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ የቦርድ አመራር አባላትና የጽ/ቤት ኃላፊ በተገኙበት ውይይት፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ ተሳትፈዋል፡፡
ውይይቱን የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ የአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸምን አስመልክቶ ውይይት ሲደረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውሰው፤ ቀደም ባለው ውይይት ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ እንደተጋበዙበትና ይህኛው ግን ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በተለየ ሁኔታ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብቻ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል። አያይዘውም የውይይቱ ዓላማ በጉዳዩ ላይ ጊዜ ሰጥቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መረዳት አንጻር የአካባቢ ምርጫን ተስፋ እና ተግዳሮት ማየት በማስፈለጉ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሰብሳቢዋ፤ በዚህም የተሻለ ግብዓት ማግኘት እንደሚቻል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ የሆኑት ፈይሰል አብዱልአዚዝ በበኩላቸው የጋራ ምክር ቤቱ ከቦርዱ ጋር በመተባበር ይህን ውይይት ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ገልጸው፤ ይህ የሚደረገው ፖለቲካ ፓርቲዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው የአካባቢ ምርጫ ላይ እንዲሣተፉና የዕውቀት ውስንነት እንዳይኖር ለማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
በማስከተል የአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸምን አስመልክቶ ጥናት ያካሄዱት ዘመላክ አየለ (ፒ.ኤች.ዲ) እና ክርስቶፍ ቫንደር (ፒ.ኤች.ዲ) ለተሣታፊዎች ጥናት አቅርበው፤ የውይይቱ ተሣታፊዎች ያላቸውን ተስፋና ሥጋት አጋርተዋል፡፡
በተጨማሪም ተሣታፊዎቹ የአካባቢ ምርጫን አስመልክቶ የቦርዱን መረዳት ጠይቀዋል፡፡ ምላሹን የሰጡት ዋና ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ እያንዳንዱ ክልልና አካባቢ የተለያየ የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ብዛት፣ የተለያየ የመንግሥት አወቃቀር ስላለው ቦርዱ እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለስኬቱ ሲባል በሁሉም ቦታዎች የአካባቢ ምርጫን በተመሳሳይ ቀን የማድረግ እቅድ እንዳልያዘ አስረድተዋል፡፡ ቦርዱ ትክክለኛ ቀኑን ባይወስንም በዚህ የበጀት ዓመት ውስጥ በአብዛኞቹ ክልሎች የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ ማቀዱንና ስለሚካሄድበት ጊዜ ዝርዝር ዕቅድ እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል።
የቀረበውን ጥናት መሠረት በማድረግ የአካባቢ ምርጫን ለማካሄድ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መውጣት ያለባቸው ሕጎች እንዲወጡ ቦርዱ እንደሚያደርግ፤ በቦርዱ የወጡ መመሪያዎቸንም ለዚሁ እንዲረዳ እንደሚሻሻሉና ራሱን የቻለ መመሪያ በቦርዱ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል። የፓርቲዎች አንዱ ትኩረት ምርጫ ማካሄድ እንዲቻል ምን በጎ አስተዋዖ እናበርክት በሚለው ላይ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።