የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አ.ብ.ን በድጋሜ የሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔን አስመልክቶ የቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ውሣኔ አሣለፈ
የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም.
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ እና መጋቢት ዘጠኝ እና ዐሥር 2014 ዓ.ም. የተካሄደውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባን አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ቦርዱ ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ከሪፖርቱ ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉና ከመተዳደሪያ ደንቡ አንጻር መርምሮ ያሣለፈው ውሣኔ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/586 በተጻፈ ደብዳቤ ለፓርቲው ገልጿል፡፡
ፓርቲው ሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በቁጥር አብን392/02/14 በተጻፈ ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሥራዎች መከናወናቸውን፣ ከነዚህ መካከል የሕገ ደንብ ማሻሻያ እንደሚገኝበት ገልጾ በቦርዱ በተሰጠው አስተያየት መሠረት ማሻሻያዎች የተደረገበት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ በጉባዔ ከመፅደቁ በፊት አያይዞ አቅርቧል፡፡
ቦርዱ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ያቀረበውን ሠነድ ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንጻር መርምሯል።
ፓርቲው ባቀረበው የተሻሻለ ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ማስተካከያ ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች፡-
1. በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 11.1.25 ማዕከላዊ ምክር ቤቱ በምዕራፍ ሁለት ከአንቀጽ ዘጠኝ- አንቀጽ 22 የተዘረዘሩትን ተግባራት እስከ ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ማሻሻል እንደሚችል ደንግጓል፡፡ ይሁንና ከእነዚሁ 14 አንቀጾች መካከል፤
- በአንቀጽ 10.1 ሥር ንዑስ አንቀጽ 10.1.1 የጠቅላላ ጉባዔ የሥራ ዘመንና፣ በንዑስ አንቀጽ 10.1.3 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ብዛትን የሚመለከቱት፤
- በአንቀጽ 10.2 የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ስብጥር የሚመለከተው፣
- በአንቀጽ 10.3 የጠቅላላ ጉባዔውን ሥልጣንና ተግባር የሚመለከተው፣
- በአንቀጽ 11.1.1 የማዕከላዊ ኮሚቴውን ተጠሪነትና አባላት ብዛትን የሚመለከተው፤
- አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 12.1.1 የብሔራዊ የኦዲትና የሕገ ደንብ ተርጓሚ ኮሚቴን ተጠሪነትና ብዛት፣ አንቀጽ 12.1.2 በሥሩ የሚያዋቅራቸውን የሕገ ደንብ ተርጓሚ ኮሚቴዎች እና 12.2.3 የራሱን የሥራ ክፍፍል መመሪያ ስለማውጣት በሚመለከቱትን፣
- አንቀጽ 12.2 ከንዑስ አንቀጽ 12.2.1 - 12.2.5 የብሔራዊ የኦዲትና የሕገ ደንብ ተርጓሚ ኮሚቴን ተግባርና ኃላፊነት የሚመለከቱት ላይ በማዕከላዊ ኮሚቴው ማሻሻያ ማድረጉ ከዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ጋር የሚቃረን በመሆኑ ከላይ በዝርዝር የተገለጹት ንዑስ አንቀጾች ለማዕከላዊ ኮሚቴ የሚሰጡ ሥልጣኖች አይሆኑም። ስለዚህ ከዚህ በላይ የተገለጹትን በማውጣት በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 11.1.25 ላይ ማስተካከያ እንዲደደረግበት፣
2. በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 24.1 ማዕከላዊ ምክር ቤቱ ዕጩ አባላትን የጠቅላላ ጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ መልምሎ እንደሚያቀርብ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የሚጠቆሙት ዕጩዎች ብዛት እና በምን መሥፈርት ዕጩዎቹ እንደሚመለመሉ መቅረብ ያለበት በመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፣
3. በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 25 መሠረት የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴው የኦዲትና ሕገ ደንብ ተርጓሚ ኮሚሽንን መልምሎ እንደሚያቀርብ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የሚጠቆሙት ዕጩዎች ብዛት እና በምን መሥፈርት ዕጩዎቹ እንደሚመለመሉ መቅረብ ያለበት በመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፣
4. በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 15.1.5 ሥራቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሥራ አስፈጻሚው አቅራቢነት ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀርቦ ኮሚቴው አጣርቶ አስተዳደራዊ ውሣኔ እንደሚያሳልፍ የሚያስቀምጥ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንቀጽ 34.1 በሥራ አስፈጻሚ ላይ የሚቀርብ ክስ በማዕከላዊ ምክር ቤት በሚቋቋም የብሔራዊ ዲሲፒሊን ኮሚቴ እንደሚታይ ይደነግጋል፡፡ ይህም እርስ በራሱ የሚቃረን እና በሥራ አስፈጻሚ ላይ የሚቀርብ ክስ በየትኛው አካል እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት።
ጠቅላላ ጉባዔውን በተመለከተ
1ኛ/ ፓርቲው እስከ ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ በቦርዱ መወሠኑ ይታወቃል። ይሁንና ፓርቲው በቦርዱ ውሣኔ መሠረት ጉባዔውን ሳያካሂድ የተሰጠው ጊዜ ገደብ አልፏል፡፡ በመሆኑም ጠቅላላ ጉባዔውን መቼ ለማድረግ እንደወሠነ ለቦርዱ በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ፣
2ኛ/ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲነጋገርበት የሚቀርቡ አጀንዳዎችን አስቀድሞ ለቦርዱ እንዲያሳውቅ፣
3ኛ/ የፓርቲው የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የሚጠሩበትን ሁኔታ በተመለከተ በፓርቲው የተሰጡ የፓርቲው ውሣኔዎችን እንዲያቀርብ እና እስካሁን ያለውን ክዋኔያቸውን እንዲያብራራ፣
4ኛ/ በተጨማሪም ሌሎች የጠቅላላ ጉባዔ ቅድመ ጉባዔ ዝግጅቶችን ለቦርዱ እንዲገልጽ ቦርዱ የወሠነ መሆኑን እናሳውቃለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም.