የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ (ካአፓ) መጋቢት 03 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ተከታዩን ውሣኔ አሣልፏል
የተወነበት ቀን ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም.
መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በቁጥር ካአፓ/1052/ በተጻፈ ደብዳቤ ፓርቲው መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ሪፖርት አቅርቧል።
ቦርዱ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ከሪፖርቱ ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና የቦርዱ ታዛቢዎች ካቀረቡት ሪፖርት አንጻር መርምሯል።
ጠቅላላ ጉባዔውን በተመለከተ
• በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ፤ የቁጥጥር ኮሚሽንና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እጅ በማውጣት መደረጉ በዐዋጅ አንቀጽ 74(3) መሠረት ሚሥጥራዊ በሆነ መልኩ ያልተደረገ የሕጉን አስገዳጅ ድንጋጌ የተቃረነ በመሆኑ ፓርቲው ሕጉን መሠረት በማድረግ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ ሊካሄድ እንደሚገባ ቦርዱ ወሥኗል፡፡
የመተዳደሪያ ደንቡን በተመለከተ
ሀ/ የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 14(2)(6) የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ቁጥር ሲጓደል ሥራ አስፈጻሚው ባለው ቁጥር እንዲቀጥል ያደርጋል የሚለው በዐዋጁ ቁጥር 74(1)(ሰ) ሥር ያለውን ዝቅተኛ ቁጥር 200 እንዳይሟላ ሊያደርግ የሚችል በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግበት፤
ለ/ በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 14.1(4) ጠቅላላ ጉባዔው በየሦስት ዓመቱ እንደሚሰበሰብ አንቀጽ 14.3 ደግሞ በየዓመቱ እንደሚሰበሰብ መደንገጋቸው የሚጋጭ መሆኑ ይኸው ተስተካክሎ እንዲቀርብ፤
ሐ/ በአንቀጽ 14.3(8) ጠቅላላ ጉባዔው ሥልጣንና ኃላፊነቱን ለማዕከላዊ ምክር ቤት በከፊል በውክልና ይሰጣል የሚለው በዐዋጁ ለጠቅላላ ጉባዔው ብቻ የተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት የሚያካትት ሊሆን ስለሚችል ለጠቅላላው ጉባዔ በብቸኝነት የተሰጡትን እንደማይጨምር በግልጽ ሊቀመጥ የሚገባ በመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፤
መ/ የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 22.1 ማንኛውም የፓርቲ ስብሰባ ከግማሽ በላይ አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ እንደሞላ ይቆጠራል የሚለው ጠቅላላ ጉባዔው ለ200 በታች ሆኖም እንዲሰበሰብ የሚፈቅድ በመሆኑ ከዐዋጁ አንቀጽ 74.1(ለ) ጋር በሚስማማ መልኩ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፤
ሠ/ በአንቀጽ 22.5 ሚሥጥራዊ ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት በተሰብሳቢ ፍላጎት እንዲደረግ ዕድል መሰጠቱ አንቀጽ 74(3) እና ከደንቡ ከደንቡ አንቀጽ 20 ጋር የሚጋጭ በመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፤
ረ/ የፓርቲው አባላት ለሀገር ዐቀፍና በየደረጃው ላሉ ሀገራዊ ምርጫዎች የሚታጩበት ሥርዓት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ ያልተካተተ በመሆኑ ማስተካከያ በማድረግ ማቅረብ እንዳለበት ቦርዱ ወሥኗል፡፡
በመሆኑም ፓርቲው በዐዋጁ መሠረት በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ እና ተሻሽሎ የቀረበው የፓርቲው መተዳዳሪያ ደንብም ከላይ ከተራ ቁጥር ሀ - ረ የተገለጹትን በሕጉ መሠረት በማካተት ሊሻሻል እና በጠቅላላ ጉባዔው ሊጸድቅ ይገባል ሲል ቦርዱ ወሥኗል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1ኛ/ ፓርቲው ይህ ውሣኔ ከተገለጸበት ከሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ፣
2ኛ/ የአመራር ምርጫን በሚመለከት ጉባዔው በሕጉ መሠረት መከናወን ያለባቸውን ሂደቶች የድምፅ አሰጣጥ፣ የድምፅ ቆጠራ እና ውጤት አገላለፅ በሕጉ መሠረት እንዲከናወኑ እንዲያደርግ፤
3ኛ/ ፓርቲው ከላይ ከተራ ቁጥር ሀ - ረ የተገለጹትን የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት ማሻሻያ የተደረገባቸው የመተዳደሪያ ደንቡን አንቀጾች የተካተቱበት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ጉባዔው ከሚካሄድበት አምስት የሥራ ቀናት አስቀድሞ ለቦርዱ እንዲያቀርብ፣
4ኛ/ ከላይ የተገለጹት ማስተካከያዎች የተደረገበት እና በቦርዱ በቅድሚያ የታየ የተሻሻለ የመተዳደሪያ ደንብ ለጠቅላላ ጉባዔው አቅርቦ በማስወሠን እንዲያቀርብ፣
5ኛ/ ፓርቲው የጉባዔው ዝርዝር ሂደት እና ውሣኔ የሚገልጽ ቃለ ጉባዔ፣ በጉባዔው የፀደቀውን መተዳደሪያ ደንብ እና የጠቅላላ ጉባዔውን ሪፖርት ጉባዔው በተካሄደ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ቦርዱ የወሠነ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም.