የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ሶሻል-ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ተከታዩን ውሣኔ አሣልፏል
የተወነበት ቀን ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም.
ሚያዚያ 10 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር ESDP/0223/2014 በተጻፈ ደብዳቤ ፓርቲው መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ሪፖርት አቅርቧል።
ቦርዱ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ከሪፖርቱ ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና የቦርዱ ታዛቢዎች ካቀረቡት ሪፖርት አንጻር መርምሯል።
የጠቅላላ ጉባዔ አካሄድን በተመለከተ
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ዕጩዎች ያገኙት ድምፅ አቆጣጠርን በሚመለከት ከቦርዱ የተላኩት ታዛቢዎች ባቀረቡት ሪፖርት ግልጽ ባልሆነ መንገድ እየተቆጠረ እንደነበር አረጋግጠው፤ የጉባዔ አዘጋጆችን ቆጠራው በትክክል ለምን እንደማይካሄድ ሲጠይቁ ጉባዔተኛው ከሩቅ የመጡ እና ሌሊቱን እስኪቆጠር መጠበቅ እንደማይችሉ እንደተገለጸላቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ “አልፈዋል/ ተመርጠዋል” የተባሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር በአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲነበብ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ቆጠራው በአግባቡ ተጠናቆ ባልተመዘገበበት ሁኔታ ከ45 ዕጩዎች ውስጥ 36 ከፍተኛ ድምፅ አግኝተዋል ተብለው የተመረጡበት አግባብ ግልጽ ያልነበረ በመሆኑ፤ ከ15-36 የተዘረዘሩት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እያንዳንዳቸው ያገኙት ድምፅ ያልተገለጸ በመሆኑ፤ በተጨማሪም የኦዲትና ኢንስፔክሽንና ኮሚቴ አባላት ምርጫ በግልጽ እጅ በማውጣት የተከናወነ በመሆኑ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና የዐዋጁን አንቀጽ 74(3) አስገዳጅ ድንጋጌ የተቃረነ ሆኖ ተገኝቷል።
ከላይ በተገለጹት የሕግ አፈጻጸም መሠረታዊ ጉድለቶች ምክንያት ቦርዱ ፓርቲው የሕጉን እና መተዳደሪያ ደንብ መርኆችን በተከተለ ሁኔታ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ ሊካሄድ እንደሚገባ ወሥኗል፡፡
የመተዳደሪያ ደንቡን በተመለከተ - በቀጣዩ ጉባዔ የሚጸድቅ
ሀ/ የፓርቲውን ገንዘብና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት፤ የገቢ ማስገኛ አሠራር በከፊል ያልተሟላ መሆኑ ተሟልቶ መቅረብ ያለበት በመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፣
ለ/ የፓርቲው ልዩ ልዩ አካላት፤ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የሚመረጡበት ሥርዓት እንዲሁም ሊቀ-መንበር፤ ም/ሊቀ-መንበር፤ ዋና ጸሐፊ እና ም/ዋና ጸሐፊ የሚመረጡበት ሥርዓት እና የአገልግሎት ዘመናቸው በመተዳደሪያ ደንቡ ያልተቀመጠ መሆኑ በማካተት መቅረብ ያለበት በመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፣
ሐ/ ፓርቲው ከሌላ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች ጋር ስለሚያደርገው ውኽደት፤ ቅንጅት ወይም ግምባር ስለሚፈጥርበት ድንጋጌ የዐዋጁ አንቀጽ 74(1) (ተ) በሚደነግገው መሠረት በመተዳደሪያ ደንቡ መካተት ያለበት በመሆኑ አስፈላጊው ማሻሻያ እንዲደረግበት፣
መ/ የፓርቲው የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ 35.4 “በማንኛውም ፓርቲው አመራር ስብሰባ የድምፅ አሰጣጥ እጅ በማውጣትና በማሳየት ይሆናል ካለ በኋላ ሆኖም በተሰብሳቢዎች ከታመነ በሚሥጥር የድምፅ አሰጣጥና ዘዴ ይከናወናል” የሚለው የዐዋጁን ድንጋጌ አንቀጽ 74/3 የአመራር ምርጫ በሚሥጥር ድምፅ መሰጠት እንዳለበት ከሚደነግገው ጋር የሚቃረን በመሆኑ ማስተካከያ በማድረግ በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ በግልጽ በማካተት ማቅረብ ያለበት በመሆኑ ተካትቶ እንዲቀርብ፣
ሰ/ የጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔ 50 + 1 እንደሆነ የተገለጸው የጉባዔውን አባላት ብዛት ከ500 በታች ስለሚያደርግው ይህ ደግሞ የሀገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ምልዓተ ጉባዔ በዐዋጁ አንቀጽ 74/1/ 500 መሆን እንዳለበት የተቀመጠውን አስገዳጅ ድንጋጌ የሚቃረን በመሆኑ፤ እንዲሁም የደንብ ማሻሻያ ምልዓተ ጉባዔ በደንቡ ውስጥ ያልተቀመጠ መሆኑ ከሕጉ ጋር ስለሚቃረን ማስተካከያ በማድረግ ማቅረብ እንዳለበት ቦርዱ ወሥኗል፡፡
በመሆኑም ፓርቲው በዐዋጁ መሠረት በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ እና ተሻሽሎ የቀረበው የፓርቲው መተዳዳሪያ ደንብም ከላይ ከተራ ቁጥር “ሀ” እስከ “ሰ” የተገለጹትን በሕጉ መሠረት በማካተት ሊሻሻል እና በጠቅላላ ጉባዔው ሊጸድቅ ይገባል ሲል ቦርዱ ወሥኗል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1ኛ/ ፓርቲው ይህ ውሣኔ ከተገለጸበት ከሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ፣
2ኛ/ የአመራር ምርጫን በሚመለከት በሕጉ መሠረት መከናወን ያለባቸውን የድምፅ አሰጣጥ፣ የድምፅ ቆጠራ እና ውጤት አገላለጽ ሂደቶች በሕጉ መሠረት በማድረግ ተሟልተው እንዲከናወኑ እንዲያደርግ፣
3ኛ/ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴን በተመለከተ የምርጫውን ሂደት የሚገልጽ የማዕከላዊ ኮሚቴ ቃለ-ጉባዔ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባው ላይ ስለመገኘታቸው የፈረሙበት ሠነድ በሚቀጥለው ምርጫ ከቃለ ጉባዔው ጋር አብሮ እንዲቀርብ፣
4ኛ/ የተመረጡትን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዝርዝርና ለመሥራት መስማማታቸውን የሚገልጽ የፈረሙበት ሠነድ ዋናው ቅጂ ከሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ጋር አብሮ እንዲቀርብ፤
5ኛ/ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን በድጋሚ ሲያደርግ ከላይ ከተራ ቁጥር “ሀ” እስከ “ሰ” የተገለጹትን የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በማድረግ ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት ማሻሻያ የተደረገባቸው የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጾች የተካተቱበት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ጉባዔው ከሚካሄድበት አምስት የሥራ ቀናት አስቀድሞ ለቦርዱ እንዲያቀርብ፣
6ኛ/ ከላይ የተገለጹት ማስተካከያዎች የተደረገበት እና በቦርዱ በቅድሚያ የታየ የተሻሻለ የመተዳደሪያ ደንብ ለጠቅላላ ጉባዔው አቅርቦ በማስወሠን እንዲያቀርብ፣
7ኛ/ ፓርቲው የጉባዔውን ዝርዝር ሂደት እና ውሣኔ የሚገልጽ ቃለ ጉባዔ፣ በጉባዔው የጸደቀውን መተዳደሪያ ደንብ እና የጠቅላላ ጉባዔውን ሪፖርት ጉባዔው በተካሄደ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ቦርዱ የወሠነ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም.