የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ፓርቲዎች ያቀረቡትን የምዝገባ ፍቃድ አስመልክቶ ተከታዩን ውሣኔ አሣልፏል
1. በእነአቶ መንግሥቱ ዩንካ ላይ
የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም.
ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት “የሲዳማ አርነት ግንባር (ሲአግ)” በሚል ስያሜ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ እንዲሰጠው ለቦርዱ አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ እነአቶ መንግሥቱ ዩንካ ያቀረቡትን የጊዜያዊ ዕውቅና ጥያቄ መርምሯል። በዐዋጁ አንቀጽ 86/1 የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜ ከተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲ ስም ጋር የማይመሳሰል ወይም በመራጮች ዘንድ መደናገር የማይፈጥር የፓርቲው ብቸኛ መጠሪያ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል።
ይሁንና “የሲዳማ አርነት ግንባር (ሲአግ)” የሚለው የፓርቲው ስም እና አኅፅሮተ ስም በቦርዱ ተመዝግቦ ከሚገኘው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ስም እና አኅጽሮተ ስም ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ ስማቸውንና አኅጽሮተ ስማቸውን ቀይረው ማመልከቻቸውን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ቦርዱ ለፓርቲው አሳውቋል።
2. በእነአቶ ጊደና መድኅን ላይ
የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም.
ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት “ትንሣዔ ሰብዓ-እንደርታ ፓርቲ (ትሰእፓ)” በሚል ስያሜ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ እንዲሰጣው ለቦርዱ አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ እነአቶ ጊደና መድኅን ያቀረቡትን የጊዜያዊ ዕውቅና ጥያቄ መርምሯል። በዐዋጁ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 65/1 መሠረት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ከሚያስፈልገው 4,000 መሥራች አባላት መካከል 60 በመቶ የክልሉ መደበኛ ኗሪዎች መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል። በተጨማሪም በዐዋጁ አንቀጽ 66/6 መሠረት የጊዜያዊ ምዝገባ ፍቃድ የሚያስፈልገው ፓርቲውን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማከናወን ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ፓርቲውን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉትን ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል ባለመሆኑ ወደፊት የተመቻቸ ሁኔታ ሲኖር የጊዜያዊ ዕውቅና ጥያቄውን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ቦርዱ ለፓርቲው አሳውቋል።
3. በእነአቶ የማንአይቶት በየነ ላይ
የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም.
ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት “የኩሽ ሕዝቦች ብሔራዊ ንቅናቄ (ኩሕብን)” በሚል ስያሜ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ እንዲሰጣው ለቦርዱ አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ እነአቶ የማንአይቶት በየነ ያቀረቡትን የጊዜያዊ ዕውቅና ጥያቄ መርምሯል። ፓርቲው ባቀረበው የዕውቅና ጥያቄ ማመልከቻ ላይ የሚያቋቁመው ፓርቲ ክልላዊ እንደሆነ የሚገልጽ ሲሆን፤ በቀረበው ሠነድ ውስጥ ደግሞ ለሀገር ዐቀፍ ወይም ለክልላዊ ስለመሆኑ፤ ክልላዊ ከሆኑም በየትኛው ክልል እንደሚንቀሳቀሱ ግልጽ አድርገው እንዲያቀርቡ ቦርዱ ለፓርቲው አሳውቋል።
4. በእነአቶ ለገሠ ማሬሮ ላይ
የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም.
ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት “የሲዳማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሲዴፓ)” በሚል ስያሜ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ እንዲሰጣው ለቦርዱ አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ እነአቶ ለገሠ ማሬሮ ያቀረቡትን የጊዜያዊ ዕውቅና ጥያቄ መርምሯል። በዐዋጁ አንቀጽ 86/1 የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜ ከተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲ ስም ጋር የማይመሳሰል ወይም በመራጮች ዘንድ መደናገር የማይፈጥር የፓርቲው ብቸኛ መጠሪያ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል።
ይሁንና “ሲዴፓ” የሚለው የፓርቲው አኅፅሮተ ስም በቦርዱ ተመዝግቦ ከሚገኘው “ሲአፓ” አኅጽሮተ ስም ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ አኅጽሮተ ስማቸውን ቀይረው ማመልከቻቸውን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ቦርዱ ለፓርቲው አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም.