የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ፓርቲዎች የሚያካሄዱትን ጠቅላላ ጉባዔ በተመለከተ የተሰጡ ማብራሪያዎችን ተመልክቶ ተከታዮቹን ውሳኔዎች አሳለፈ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ፓርቲዎች ከሚያካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ጋር በተያያዘ ተከታዮቹን ውሳኔዎች አሳልፎ ለፓርቲዎቹ አሳውቋል።
1. የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር/ኦብነግ
የተወሰነበት ቀን፦ ሚያዝያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም
ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን ከሚያዝያ 22-24 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚያደርግ ለቦርዱ በመግለጽ የጠቅላላ ጉባዔውን ዝግጅት የሚያሳይ መረጃ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ቢያቀርብም፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 8.5 መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ መወሰን ያለበት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በመሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ የወሰነውን ውሳኔ ዝርዝር የሚያሳይ ቃለ ጉባዔ ደብዳቤ በደረሳቸው በ5 ቀን ውስጥ አሟልተው እንዲያቀርቡ ቦርዱ ለፓርቲው ሊቀመንበር በጽሑፍ አሳውቋል።
በሌላ በኩል የኦብነግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አሕመድ ያሲን መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም የፓርቲው ሊቀመንበር የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ በ19 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በቀረበ ጥያቄ በየካቲት 19 ቀን 2014 ዓ.ም (Feb 25/2022) በኢሜል ብንልክም ሊቀመንበሩ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸው መተዳደሪያ ደንቡን ይጥሳል ሲሉ ለቦርዱ ነጥቡን ያስረዳል በሚል ያቀረቡት ሰነድ በርግጥም የኢሜል ልውውጥ በጉዳዩ መደረጉን የማያሳይ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የፓርቲው ም/ሊቀመንበር፣ ሊቀመንበሩ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠሩ ተጠይቀው ፍቃደኛ አለመሆናቸውን በተመለከተ አለ የተባለውን ማስረጃ ደብዳቤ በደረሳቸው በ5 የስራ ቀን አሟልተው እንዲያቀርቡ ቦርዱ አሳውቋል።
2. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
የተወሰነበት ቀን፦ ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሚያዚያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፣ በመጪው ሰኔ ወር 2014 መደበኛ ጉባዔውን እንደሚያካሄድ በመግለጽ የፓርቲው መሪ እና ምክትል መሪ የኃላፊነት ጊዜያቸው ቢያበቃም የመሪ እና የምክትል ምርጫውን በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ለማካሄድ የሚያስቸግር ስለሆነ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 7.1.1፣ 18.3.3 እና 18.3.2 ለጊዜው ከመፈጸም ታግደው እንዲቆዩ እና የፓርቲው መሪ እና ምክትል መሪ ለአንድ ጊዜ ብቻ እንደ ሌሎች የጉባኤ ተመራጭ ኃላፊዎች እንዲመረጡ በሙሉ (የተባበረ) ድምጽ ስለወሰነ በሚል ሥራ አስፈጻሚው ለጠቅላላ ጉባኤው ለማቅረብ ያዘጋጀውን የውሳኔ ሐሳብ ሰነድ ለቦርዱ አያይዞ አቅርቧል።
ቦርዱ ጉዳዩን መርምሮ ከዚህ የሚከተሉት በፓርቲው እንዲፈጸሙ አሳውቋል፦
የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከላይ የተገለጸውን ውሳኔ ያሳለፈበትን ቃለ ጉባኤ እንዲቀርብ
ለቦርዱ ከቀረበው በተጨማሪ ለጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የሚቀርብ የደንብ ማሻሻያ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጸድቆ ከሆነ ሰነዱ እንዲቀርብ
ቦርዱ ፓርቲው መስከረም 22 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ያደረገውን የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ በተመለከተ የሰጣቸውን የውሳኔ ነጥቦች፣ የተወሰዱ ርምጃዎች እና የተዘጋጀ የደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ካለ ሰነዱ እንዲቀርብ
ቦርዱ ታዛቢዎችን በአዋጁ አንቀጽ 79/2 መሠረት መላክ ይችል ዘንድ ጠቅላላ ጉባኤ የሚደረግበት እንዲገለጽ
3. ለዎላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ሊቀመንበር
የተወሰነበት ቀን፦ ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም
የፓርቲው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ የፓርቲው አመራሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት የፓርቲው ሊቀመንበር ጉባኤውን ለመጥራት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው እንዲሁም የተፈጠረው አለመግባባት የግንባሩን ሕልውና የሚያናጋ እና አስጊ ወደሆነ አቅጣጫ የሚያመራ በመሆኑ ችግሩን በጉባኤ ለመፍታት ጉባኤ መጥራት የወሰነ እና የቦርዱ ታዛቢ እንዲላክለት በተለያየ አቤቱታ አሳውቋል፡፡
በፓርቲው ደንብ መሠረት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት የሚችለው ለፓርቲው ሊቀመንበር በቅድሚያ አስቸኳይ ጉባኤውን እንዲጠራ ካሳሰበ እና ሊቀመንበሩም ይህን ተከትሎ አስቸኳይ ጉባኤውን ለመጥራት ፍቃደኛ ያልሆነ ከሆነ ነው፡፡
በመሆኑም ቦርዱ የፓርቲው ሊቀመንበር በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት እስከ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲጠሩ፥ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ስላደረጉት ዝግጅት እንዲሁም ጉባኤውን ለመጥራት ያለውን ዝርዝር እቅድ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ይህ ካልተፈፀመ በፓርቲው መተዳደሪያ መሠረት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አስመራጭ ኮሚቴና ጊዜያዊ ሊቀመንበር በመሠየም ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ሥልጣን ያለው መሆኑን ቦርዱ ለፓርቲው ሊቀመንበር እና ለኢንስፔክሽን ኮሚሽኑ ቦርዱ ገልጿል፡፡
4. ለአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)
የተወሰነበት ቀን፦ ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም
አትፓ ከቦርዱ በተጻፈ ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት የተወሰኑ ውሳኔዎች በፓርቲው ደንብ መሠረት መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ በየትኛው አካል እንደተወሰነ ማብራሪያ እና የውሳኔው ቃለ ጉባኤ እንዲሁም የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አባላት የተመረጡበት ዝርዝር ሥርዐት እና የጉባኤ አጀንዳ እንዲያቀርብ ተገልጾለታል፡፡
ፓርቲው በበኩሉ ጠቅላላ ጉባኤውን አስመልክቶ መሟላት ያለባቸው ነጥቦችን በተመለከተ አስቸኳይ የማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ መጋቢት 10 እና ሚያዝያ 5 ቀን 2014 ዓ.ም እንዳደረገ ገልጾ የስብሰባውን ቃለ ጉባኤ እና የለቀቁ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ዝርዝር አያይዞ አቅርቧል፡፡
ሆኖም የቀረቡት ቃለ ጉባኤዎች በቦርዱ እውቅና ባገኙ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምልዐተ ጉባኤ በማሟላት የተደረገ ስብሰባ አለመሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡ ቦርዱ ጉዳዩን መርምሮ በደንቡ መሠረት የተሟላ የማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ በመስጠት እስከ ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደረግና ከጠቅላላ ጉባኤ አንድ ሣምንት በፊት የጠቅላላ ጉባኤውን ዝግጅት በሚመለከት የማዕከላዊ ኮሚቴው ያደረገውን ስብሰባ ቃለ ጉባኤ ተያይዞ እንዲቀርብ በጽሑፍ አሳውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም.