Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አካሄደ። ምክክሩን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳና የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ የመሩት ሲሆን፤ በምክክሩም የፖለቲካ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ተከትሎ በአባላቶቻቸውና በአመራሮቻቸው አግባብ ያልሆነ እሥር እና እንግልት እንደተፈፀመ በመግለፅ ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት የቦርዱ ተወካይ ሰብሳቢ፣ የአቤቱታ አቅራቢ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እና የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ አባል የተካተቱበት አጣሪ ቡድኖች ተቋቁመው የቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት አቤቱታ ወደቀረበባቸው ክልሎች በመንቀሳቀስ እንዲያጣሩ መደረጉን ተከትሎ የተገኙ ውጤቶችን ተመልክተዋል።
ቦርዱ ለተከታታይ ሳምንታት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ምክክር አጣሪ ቡድኖቹ የደረሱበትን ሲያሳውቅ ቆይቷል። በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፌዴራል ፖሊስ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን/በኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ ማቆያ ቤት ከሚገኙ የፓርቲ አመራሮችና አባላት መካከል የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው የተፈቱ መሆኑን፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አምስቱም አባላቱ የተፈቱ መሆኑን፤ ባጠቃላይ አጣሪ ቡድኑ ሥራ ሲጀምር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማቆያ ቤት ከሚገኙት 23 አባላት መካከል 20 ተፈተው የቀሩት ሦስት ሰዎች ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኤዴኅ) ፓርቲው አባል የተፈቱ መሆኑን፣በማቆያ ቤት ከሚገኙት 492 የቤሕነን አባላት መካከል 256ቱ መፈታታቸውን እና በቀጣይም ተጨማሪ 192 የፓርቲው አባላት በቅርብ ቀን እንደሚለቀቁ፤ በእሥር ላይ የነበሩ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) 34ም (ሁሉም) አባላቱ በዋስ እንደተለቀቁ፤ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) አባላትም እንዲሁ በሙሉ በዋስ የተለቀቁ መሆኑን ተገልጿል።
በውይይቱ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሰጡት አስተያየት ቦርዱ በማቆያ ቤት የሚገኙትን የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራርና አባላትን ለማስፈታት እያደረገ ያለውን ጥረትና እያስገኘ ያለውን ውጤት ያደነቁና ያመሰገኑ ሲሆን፤ የእሥረኞች አያያዝና ክስ በሕጉ መሠረትና በወቅቱ ያለመመሥረት እንዲሁም ሕክምና የማግኘት ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። አያይዘውም ከታች ያለው የመንግሥት ከፍተኛ የሕግ ጥሰትና መጉላላት እንዳለ አቤቱታ አቅርበዋል።
ቦርዱ ቀሪ ያልተፈቱ እሥረኞን በሚመለከት የሚያደርገው ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ እሥረኞች የት እንደሚገኙ መረጃ ሲኖር ተከታትሎ የማስፈታት ሥራ፤ የት እንደሚገኙ የማይታወቁትን ደግሞ የማጣራት ሥር በማድርግ የታሠሩበትን ቦታ በመለየት የሚፈቱበትን አግባብ ላይ እየተሠራ እንደሚገኝ፤ እስከዛው ግን በቤተሰብ እንዲጎበኙና በቂ ሕክምና እያገኙ መሆኑን፤ የአያያዝ ችግር እንደሌለ የማረጋገጥ ሥራን ለማከናወን እየጣረ እንደሆነ አስታውቋል።
በዕለቱም በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለሳምንታት ሃሳብ እየተሰጠበት ማሻሻያዎች ሲደረግበት የነበረው “በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውይይት የሚመራበት መመሪያ” ተጠናቆ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተወካዮች ተፈርሞበት ጸድቋል።

ይህንኑ በፓርቲዎች የተፈረመበት መመሪያ እዚህ ላይ ያገኙታል

Share this post