የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በሐረሪ ክልል፣ በሶማሌ ክልል እና በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል እየተካሄደ ያለው ምርጫ በሰላም እየተካሄደ እንደሆነ ገለጹ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በሐረሪ ክልል፣ በሶማሌ ክልል እና በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል እየተካሄደ ያለው ምርጫ በሰላም እየተካሄደ እንደሆነ ለብዙኃን መገናኛ አካላት ገለጹ። ቦርዱ ከምርጫ ጣቢያዎች፣ ከምርጫ ክልሎች፤ ከተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቸ እንዲሁም ከታዛቢዎች የሚመጡለትን ሪፖርቶች እየተቀበለ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ እንዳለ የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ከነዚህም ውስጥ ሶማሌ ክልል ፊቅ ምርጫ ክልል የሚገኙ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቶቻቸው በውኃ በመበላሸታቸው ከመጠባበቂያ ላይ መጠቀማቸው፣ ሞያሌ ላይ ድኩቺ ምርጫ ጣቢያ ድምጽ አሰጣጥ ከመቋረጡ ውጪ መሰረታዊ የሆነ ችግር እንዳልገጠመ ገልጸዋል። እንዲሁም ዳውሮ ዞን የሲቪል ማህበራት ታዛቢ ለአጭር ጊዜ ታሥሮ የነበረ መሆኑ (አሁን ተፈቷል) ከቀረቡት ሪፖርቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
በአጠቃላይ የቁሳቁስ ሥርጭትን የተመለከተ የገጠመ ችግር የሌለ ሲሆን፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቅሬታ ሪፖርቶች ቀርበው ቦርዱ እየፈታላቸው እንዳለ ተገልጿል። በአጠቃላይ ሲታይ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ ዋና ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ አስረድተዋል። ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ፓለቲካ ፓርቲዎችን፣ ጸጥታን የተመለከቱ ጥያቄዎችንም መልሰዋል።
የምርጫው እለት መጠናቀቅን አስመልክቶ ዕለታዊ መግለጫ አመሻሽ 12:00 ሰዓት ላይ የሚኖር ሲሆን፤ ከታች የተጠቀሱትን መሥፈርቶች የምታሟሉ ብዙኃን መገናኛ አካላት በስካይ ላይት ሆቴል ተገኝታችሁ መዘገብ የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን።
•በኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን የተመዘገበ የብዙኃን መገናኛ ተቋም መሆን፣
•የመጡበትን ብዙኃን መገናኛ መታወቂያ መያዝ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም.