በሶማሌ ብሔራዊ ክልል ስለሚደረገው የመራጮች ምዝገባ አቤቱታ ማጣራት የተሰጠ ማስታወሻ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዝያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በሶማሌ ብሔራዊ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ጉልህ የአሰራር እና የህግ ጥሰቶች አሉት በሚል አቤቱታ እና ማስረጃ ማቅረባቸውን፣ እንዲሁም የቀረቡት አቤቱታዎች እና ማስረጃዎች መሰረት አድርጎ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ መገንዘቡን እና በዚህም መሰረት መጣራት እነደሚገባቸው በማመን በሰባት የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ በመወሰን የምዝገባ ሂደቱ ላይ የቀረቡ አቤቱታዎችን ማጣራት እንደሚያከናውን ማሳወቁ ይታወሳል።
ከዚያ በመነሳትም የባለሞያዎች በመመልመል፣ ቡድን በማቋቋም፣ ቡድኑ የሚሰራበትን የአሰራር ደንብ በማዘጋጀት የምርመራው ሂደት የሚመራበትን መንገድ አጠናቆ አጣሪ ቡድኖችን በማሰማራት ሂደት ላይ ይገኛል። የአጣሪ ቡድኑን በማሰማራት ወቅት ባደረገው የመጨረሻ ማጣራትም በመጀመሪያ ከተገለጹት ሰባት ምርጫ ክልሎች በተጨማሪ አራት ምርጫ ክልሎች ላይ አቤቱታዎች ቀድመው የቀረቡ ቢሆንም ሳይገለጹ እንደቀሩ ተረድቷል።
በመሆኑም እነዚህን ምርጫ ክልሎች (ፊቅ ምርጫ ክልል፣ ገላዲን ምርጫ ክልል፣ ደገሃቡር ምርጫ ክልል እና ጂግጂጋ 2 የምርጫ ክልል) ጨምሮ በአጠቃላይ 11 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርመራውን የሚያከናውን መሆኑን እየገለጸ ስራውን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ምርጫ ክልሎቹ ላይ ለብሔራዊ ምርጫ በተቀመጠው ቀን መሰረት ድምጽ የመስጠት ሂደቱ እንዲከናወን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል።
ቦርዱ በአስር ቡድኖች የተከፈለውን የምርመራ ቡድን የስራ ውጤትም በአፋጣኝ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን ያሳውቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም