ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባን አስመልክቶ የቀረቡ አቤቱታዎች እና የተሰጡ ምላሾች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች በተመዘገቡ እጩዎች ላይ ያላቸውን ቅሬታ እና አቤቱታ ሲቀበል መቆየቱ ይታወሳል። በዚህም መሰረት ዋና ዋናዎቹ ውሳኔ የተሰጠባቸው አቤቱታዎች የሚከተሉት ናቸው።
1. የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ በወላይታ ዞን አቃቤ ህግ በእጩነት ተመዝግበዋል ብሎ አቤቱታ የቀረበው ጥያቄ ቦርዱ ተቀብሎ ለብልጽግና ፓርቲ የአቃቤህግነት ስራቸውን መልቀቃቸውን ወይም አቃቤ ህግ መሆን አለመሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቦርዱ ጠይቋል።
2. የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብልፅግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩዎች መካከል የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ሀላፊ እንደሆኑና ይህም ከሕጉ ጋር እንደሚቃረን በመግለፅ አቤቱታ አቅርበዋል። በዚህም መሰረት ቦርዱ ለብልጽግና ፓርቲ እጩው ስራውን መልቀቅ እንዳለባቸው ወይም እጩነታቸውን መተው እንደሚገባቸው ወስኖ ለፓርቲው አሳውቋል።
3. የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብልፅግና ፓርቲ በአኮቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ፣ በአቦቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ፣ እንዲሁም በአቦቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት የክልሉ ሚሊሺያ ጽ/ቤት ሀላፊ መሆናቸውን እና ይህም ከሕጉ ውጪ መሆኑን በመግለፅ አቤቱታ አቅርቧል። ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ እና ህጉን ተመልክቶ ተቀባይነት እንደሌለው በመወሰን ለፓርቲው አሳውቋል።
4. ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሴያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በቀረበ አቤቱታ ብልፅግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 31 በተደነገገው መሠረት ለእጩነት የሚያበቁ መመዘኛዎችን ተወዳዳሪው እንደማያሟሉ እና በምርጫ ክልሉ ለረጅም አመታት በስራም ሆነ በትምህርት ምክንያት እንዳልነብሩ በመግለፅ አቤቱታ አቅርበዋል። ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ፤ ተወዳዳሪው በምርጫ ክልሉ መስፈርቱን ስለማሟላታቸው ተረጋግጦ በእጩነት ተመዝግበው ሠርተፍኬት የተሰጣቸው በመሆኑ እና ፓርቲው አቤቱታውን በወቅቱ ባለማቅረቡ አቤቱታው በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን ለፓርቲው በደብዳቤ አሳውቋል።
5. ኢሶዴፓ በሌላ አቤቱታ ለቦርዱ ባስገባው ደብዳቤ የብልፅግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት በ2005 የአካባቢ ምርጫ የማረቆ ወረዳ ምክር ቤት በቆሼ አካባቢ ቀ/ገ/ማ የወረዳ ምክር ቤት ተመርጠው የነበሩ እና አሁን ደግሞ የወረዳ ምክር ቤት አባል እና የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በመስራት ላይ እንደሚገኙ በመግለፅ ከሕጉ ጋር ስለሚቃረን እንዲሰረዙ በማለት አቤቱታ አቅርቧል። ቦርዱ አቤቱታውን በመመርመር እጩ ተወዳዳሪው የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው መስራታቸው እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ከመቅረብ የሚያስቀራቸው ባለመሆኑ ፓርቲው ያቀረበው አቤቱታ በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን ለፓርቲው አሳውቋል።
6. የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ለቦርዱ ባስገባቸው ሁለት አቤቱታዎች በሰዳል ምርጫ ክልል የቀረቡ እጩ አድራሻቸው እንዲሁም የትውልድ ቦታቸው ከዚህ ምርጫ ክልል ውጪ መሆኑን በመግለፅ ከእጩነት እንዲሰርዙ፤ እንዲሁም ሌሎች እጩዎች ከማሽ ዞን ያሶ/ዛይ ወረዳ ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ የዞኑ ብልፅግና ሀላፊ በመሆናቸው ፣ እንዲሁም የቡለን ምርጫ ክልል ተወዳዳሪ የክልሉ የፀረ-ሙስና ባለሙያ በመሆናቸው እንዲሰረዙ በማለት አቤቱታ አቅርቧል። ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ የመጀመሪያው እጩ በምርጫ ክልሉ መስፈርቱን ስለማሟላታቸው ተረጋግጦ በእጩነት ተመዝግበው ሠርተፍኬት የተሰጣቸው በመሆኑ እና ፓርቲው አቤቱታውን በወቅቱ ባለማቅረቡ፣ እንዲሁም ሌሎቹ ሁለት እጩዎች የተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች በሕጉ መሠረት ከእጩነት የሚያስቀሩ ባለመሆናቸው አቤቱታዎቹ በቦርዱ ተቀባይነት ያለገኙ መሆኑን ለፓርቲው በደብዳቤ አሳውቋል።
7. ብልፅግና ፓርቲ ለቦርዱ ባቀረበው አቤቱታ የአፍዴር ዞን ምርጫ አስተባባሪ የሆኑት የቦርዱ ሰራተኛ አባታቸው እጩ መሆናቸውን በመጥቀስ ተቃውሞ አቅርቧል። ቦርዱም ይህን አቤቱታ መርምሮ የምርጫ አስፈጻሚውን ጉዳይ፣ አስፈጻሚዎች ግምገማ በሚያደርግበት ወቅት በመገምገም እርምጃ እንደሚወስድ እጩው ግን በእጩነት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ለፓርቲው አሳውቋል።