የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ዋና ተግባር የሆነው የመራጮች ምዝገባን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም ሂደት በመጀመሪያ ሰሞን የነበረው የመራጮች ምዝገባ መቀዛቀዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት በተሰበሰበው መረጃ (ያለፉት ሶስት ቀናትን ሳይጨምር) 28,731,935 ያህል መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን የመራጮች ምዝገባ በ 41,798 ያህል ምርጫ ጣቢያዎች እየተከናወነ ይገኛል።
የመራጮች ምዝገባ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በተጨማሪ ለ15 ቀን ተጨምሮ ከአፋር እና ከሶማሌ ክልሎች ውጪ የማጠናቀቂያ ጊዜው በዛሬ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሆን ማሳወቁ ይታወሳል። በዚህ ወቅትም
1. የመራጮች ምዝገባ በተራዘመበት ወቅት ተደራራቢ የበአላት ቀናት መኖራቸው እና በዚያም የተነሳ በህጉ መሰረት ብሔራዊ በአላት ዝግ በመሆናቸው የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን አለመቻሉን
2. የመራጮች ምዝገባ በተራዘመበት ወቅት 1500 መራጮች የመዘገቡ ጣቢያዎቸን ለይቶ ንኡስ ጣቢያዎችን የማደራጀት ሂደት ጊዜ መውሰዱን በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የመራጮች መጨናነቅ ምርጫ ጣቢያ ላይ መፈጠሩን ተረድቷል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የመራጮች ካርድ በመውሰድ መምረጥ የሚችሉ ቀላል የማይባሉ ዜጎች በዚህ የተነሳ የመራጮች ካርድ አለመውሰዳቸውን ቦርዱ በመገንዘብ ባደረገው ስብሰባ የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ይጠናቀቅባቸው በነበሩ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ በአማራ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በሃረሪ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በሲዳማ ክልል የመራጮች ምዝገባ እስከ አርብ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለተጨማሪ 07 ቀናት እንዲከናወን ወስኗል።
በዚህም መሰረት በእነዚህ የከተማ መስተዳድሮች እና ክልሎች የሚገኙ መራጮች የመራጭነት ካርዳቸው በነዚህ ቀናት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እንዲወስዱ እያሳወቅን፣ የቦርዱ አስፈጻሚዎች እና አስተባባሪዎች በህጉ መሰረት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀናት እስከ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የመራጮች ምዝገባን እንዲያከናውኑ እናስታውቃለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም