የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደትና የቴክኒክ ሥራዎችን የተመለከተ ውይይት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንትና የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደትና የቴክኒክ ሥራዎችን የተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መገናኛ ብዙኃን በተገኙበት ውይይት አድርጓል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በተገኙበት የተደረገው ውይይት በዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ላይ ያጋጠሙ የተለያዩ ግኝቶች የቀረቡበት ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደት የቀረቡ አቤቱታዎችና የተሰጡ መፍትሔዎች በዝርዝር በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ቀርበዋል።
ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት ላይ አቤቱታዎች እንደቀረቡ በመጥቀስ ለገዥው ፓርቲ መመሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኙት የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ገዥው ፓርቲ ከቀድሞ ልማዶች መላቀቅ እንደሚገባው ገልጸዋል። ፖለቲካ ፓርቲዎችም ማንኛውም ዕክል ሲገጥማቸው በሰዓቱ ለቦርዱ ቢያሳውቁ በጊዜ መልስ እየሰጡ ለመሄድ እንደሚያስችል በማሳሰብ፤ ፓርቲዎቹ ቦርዱ ካዘጋጀው የጥሪ ማዕከል በተጨማሪ ይቀለናል በሚሉት መንገድ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡ ቦርዱ አፋጣኝ መልስ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል። የቦርድ ሰብሳቢዋን ሀሳብ የተጋሩት ተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ መፍትሔ አገኝተንባቸዋል ያሏቸውን አካባቢዎች በመግለጽ ያመሰገኑ ሲሆን፤ አሁንም ከፍተኛ ሥጋት አሉባቸው ያሏቸውን ቦታዎች በመግለጽ በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠማቸውን እና መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮችን፣ የምረጡኝ ዘመቻ ለማድረግ የሚያስቸግሩ ያሏቸውን ሁነቶች አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ የቦርዱ የመረጃ ማዕከል በዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ውስጥ ያለው አሠራር በቦርዱ የኮሚኒኬሽን ክፍል ባልደረባ ሲቀርብ፤ የቦርዱ የአጭር መልዕክት መቀበያ የአሠራር ሥርዓት ደግሞ በቦርዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ባልደረባ ቀርቧል። ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቦርዱ ጊዜው የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም ዘመናዊ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያደርገውን ጥረት ቢያደንቁም በአፈጻጸም ወቅት ግን የተለያዩ የቴክኒክ ዕክሎች እየገጠሟቸው እንዳለ አሳስበዋል።
በጉዳዩ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ መልስ የሰጡበት ሲሆን፤ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ክፍተት በሚኖር ጊዜ መረጃውን በጽሑፍ በመሠነድ ሥራው እንደሚከናወን በማድረግ ወደ ዲጂታል ሲስተም ውስጥ የማስገባት ሥራውን በማዘግየት ሊስተናገዱ የሚችሉበት አማራጭ እንዳለ ጠቁመዋል። ከተሣታፊዎች ለተነሡት ጥያቄዎች ከቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በተጨማሪ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በዝርዝር የሰጡ ሲሆን፤ የቀረቡ አቤቱታዎችንና ምላሽ የተሰጠባቸውን እንዲሁም ቦርዱ ክትትል እያደረገባቸው ያሉትን አቤቱታዎች እንዳሉ በመጥቀስ፤ ከውይይቱ አንድ ቀን በፊትና በውይይቱ ቀን ቦርዱ ባደረገው ክትትል ከእሥር የተፈቱና ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ፓርቲያቸውንና ስማቸውን በመጥቀስ ጭምር አሳውቀዋል።
በሦስት ዙር የተሣታፊዎች ሀሳብ የተወሰደ ሲሆን በመንግሥት ላይ ለቀረቡት አቤቱታዎች ገዥው ፓርቲን በመወከል የተገኙ ተሳታፊም የገዥው ፓርቲ በመድረኩ የቀረቡ አቤቱታዎችን ሊፈቱ የሚችሉ ነው ያሉትን ስራዎች እየሰራ መሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ የተለያዩ መድርኮችን በማዘጋጀት የኦፕሬሽን ሥራዎችን ቅደም ተከተል የጠበቀ መድርኮችን እያካሄደ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየመከረ መሆኑ ይታወቃል፣ ከምክክሮቹም ይህ አራተኛው ነው።