የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴቶችን ያማከለ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እና የባለድርሻ አካላት ሚናን አስመልክቶ የምክክር መድረክ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ሴቶችን ያማከለ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እና የባድርሻ አካላት ሚናን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ። መድረኩን የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በንግግር የከፈቱት ሲሆን፤ ሰብሳቢው በንግግራቸው ያለፉት 30 ዓመታት የሴቶችን የፖለቲካ ተሣትፎ ምን እንደሚመስል ገልጸው ያለውን መሻሻል ጥናቶችን ጠቅሰው አብራርተዋል። መሻሻል ቢኖርም እንኳን ከሚፈለገውና ሊሆን ከሚገባው አንጻር እጅግ ብዙ እንደሚቀር አክለው ገልጸዋል።
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢን ንግግር ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጥናት ያጠኑት አቶ ኤልያስ ዓሊ በፖለቲካና በምርጫ ሂደቶች የሚሣተፉ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ ሲያቀርቡ፤ ከሥርዓተ-ፆታ ኦዲት ሪፖርት በኋላ ስለተገኙ መረጃዎች እንዲሁም የሴት ፓርቲ አባላት እና ዕጩዎችን አስመልክቶ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች የተመለከተ ጽሑፍ ደግሞ የቦርዱ የሥርዓተ-ፆታ እና አካታችነት ኃላፊ የሆኑት መድኃኒት ለገሠ አማካኝነት ቀርቧል።
ሴቶችን ያማከለ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ለማስቻል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የቦርዱ አመራር የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ያብራሩ ሲሆን፤ ማብራሪያቸውን ተከትሎ በአመራሯ አወያይነት ከተሣታፊዎች ሃሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል። ተሣታፊዎቹ ተመሳሳይ መድረኮች መዘጋጀት ከጀመሩ ወዲህ የአመለካከት ለውጦች መኖራቸውን በመግለጽ የቦርዱን ጥረት ያደነቁ ቢሆንም መሬት ላይ ያለው እውነት ግን ብዙ ይቀረዋል ሲሉ አሳስበዋል። ተሣታፊዎቹ ይህንንም ሲያብራሩ በዕጩ ምዝገባ ወቅት ያጋጠማቸውን ተመክሮ በማስታወስ፤ ሴት ዕጩዎቻችን ከተመዘገቡ በኋላ ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው ራሳቸውን ከዕጩነት እንዲያሰናብቱ የሚያደርግ ሁኔታዎች እየገጠሟቸው እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል። የቦርድ አመራሮቹ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ጠንካራና ተጨባጭነት ያላቸው ሃሳቦች ከተሣታፊዎች እንደተነሡ ገልጸው፤ እየተዘጋጁ ያሉ መድረኮች በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ማስቻላቸውን ማሳያ ነው ብለውታል።
ሴት ዕጩዎች የምርጫ ዘመቻውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል መወሰድ የሚችሉ እርምጃዎን እንዲሆም በምርጫ ወቅት ሊደርስ ስለሚችሉ ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ባላቸው ባለሞያ የቀረበ ሲሆን፤ በማስከተልም የሕግና የሥርዓተ-ፆታ ባለሙያ እና ዓለም ዐቀፍ አማካሪ በሆኑት መስከረም ገስጥ አወያይነት፤ ቆንጂት ብርሃኑ (የኢሕአፓ ሊቀመንበር)፤ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) (የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ) እና ነቢሃ መሐመድ (የሴት ፖለቲከኞች የጋራ ም/ቤት መሥራች አባል) የተሣተፉበት እንዲሁም ተሞክሯቸውን ያካፈሉበት የፓናል ውይይት ተደርጎና በድጋሚ የተሣታፊዎች አስተያየት ተወስዶ የመድረኩ ማብቂያ ሆኗል። መድረኩን በንግግር የዘጉት የቦርዱ አመራር ብዙወርቅ ከተተ ሲሆኑ፤ መድረኩ እንዲዘጋጅ ድጋፍ ላደረጉ አካላት እንዲሁን ለተሣታፊዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።