የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመራጮች ምዝገባ ያለውን የቁሳቁስ ዝግጅት አስጎበኘ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመራጮች ምዝገባ ያለውን የቁሳቁስ ዝግጅት ለብዙኃን መገናኛ አካላት አስጎበኘ። በቦሌ ዐየር ማረፊያ ካርጎ በሚገኘው የቦርዱ ጊዜያዊ መጋዘን በመከናወን ላይ ያለውን አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሥራ ምን እንደሚመስል ማስተዋወቅ ዐላማው ያደረገው ጉብኝት፤ በቦርዱ የኮሚኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ገለጻ የተጀመረ ሲሆን፤ ኃላፊዋ ቦርዱ ለመራጮች ምዝገባ ያለውን አጠቃላይ ዝግጁነት የሎጂስቲክና የሎጂስቲክ ሥርጭት ዕቅድ አወጣጡን ጨምረው አብራርተዋል።
ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ በመጋዘኑ ያለውን የሎጅስቲክ እንቅስቃሴ ደግሞ የቦርዱ የሎጂስቲክ ድልድልና ሥርጭት ባለሙያ ማብራሪያ የሰጡበት ሲሆን፤ በየምርጫ ጣቢያው የሚሠራጩት እያንዳንዱ ሣጥን ውስጥ የሚኖሩትን የመራጮች ምዝገባ ሊስት፣ ማኅተም ከነመርገጫው፣ የጽሕፍት መሣሪያ ኪቶች፣ ቃለ ጉባዔ መያዣና የሪፖርት መሠነጃ ቅጾች፣ ታብሌቶች፣ የፊት መሸፈኛ ጭምብልና ሳኒታይዘሮች፣ ለመራጮች በቀላሉ መረጃ ለማግኘት እንዲያስችሉ ተደርገው የተዘጋጁ ፖስተሮች እንዲሁም የቅሬታ አፈታትን የሚደነግጉ መረጃዎችን አንድ በአንድ በማሳየት ጭምር ዝርዝር ይዘታቸውን አስረድተዋል። የባለሙያውን ማብራሪያ ተከትሎ መጋዘኑ ውስጥ የሚከናወነውን እሸጋ፣ ምደባ እና ስርጭት ስራ ብዙኃን መገናኛ እንዲጎበኙት ተደርጓል።