Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የብዙኃን መገናኛ አጠቃቀምና ድልድልን አስመልክቶ የሁለት ቀን ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. እና መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የብዙኃን መገናኛ አጠቃቀምና ድልድልን አስመልክቶ ውይይት አካሄደ። የመጀመሪያው ቀን ውይይት ከብዙኃን መገናኛ ኃላፊዎች ጋር የተደረገ ሲሆን፤ መድረኩን የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ባደረጉት ንግግር ተከፍቷል። ውብሸት በንግግራቸው ለታሣፊዎቹ የመድረኩን ዐላማ አስረድተው፤ የብዙኃን መገናኛ አካላት በዐየር ሰዓት ድልድል አጠቃቀም ላይ ፓርቲዎቹን በፍትሐዊነት እንዲያስተናግዷቸው አሳስበዋል። የምክትል ሰብሳቢውን ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የሕግ ክፍል ባልደረባ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የብዙኃን መገናኛ አጠቃቀምና ድልድልን መመሪያ ቁጥር 12/2013ን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ብሔራው ምርጫ ቦርድ የኮምኒኬሽን ኃላፊና በብሮድካስት ባለሥልጣን የሥራ ክፍሎች አማካኝነት የሁለቱን ተቋማት ከብዙኃን መገናኛ አጠቃቀምና ድልድል እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ያላቸውን የኃላፊነት ድርሻ ምን አንደሆነና የዐየር ሰዓት ድልድሉ ያለፉ ምርጫ ተሞክሮዎችን፣ የብዙኃን መገናኛ ብዛት እና ዐቅም መሠረት አድርጎ እንደተሠራ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። የተሰጠው ማብራሪያ ላይ የብዙኃን መገናኛ ኃላፊዎቹ አስተያየት የሰጡበት ሲሆን፤ የተነሱ ጥያቄዎችም ተመልሰዋል።

የሁለተኛው ቀን የተደረገው ውይይት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የብዙኃን መገናኛ አጠቃቀምና ድልድልን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የብዙኃን መገናኛ በተገኙበት የተደረገ ሲሆን፤መድርኩን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በንግግር ከፍተውታል። የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቦርዱ አመራር የሆኑት ፍቅሬ ገ/ሕይወት በቦርዱ በየደረጃው የተሰጡ የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠናን አሰመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዋና ሰብሳቢዋ በበኩላቸው የመራጮች ምዝገባ ሂደት ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ ያብራሩ ሲሆን፤ በተፈለገው ጊዜ ምዝገባ የጀመሩ ጣቢያዎችንና ያጋጠሙ ውሥንነቶችን ገልጸው፤ የመራጮች ምዝገባ ከዕጩዎች ምዝገባ የተሻለ ጊዜ ስላለው በሥራው ሂደት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን እያረሙ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችል፤ ለዚህም ፓርቲዎች የሚያጋጥሟቸውን ክፍተቶች በተገቢው ጊዜ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል።

በማስከተል በተከታታይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የብዙኃን መገናኛ አጠቃቀምና ድልድልን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍን አስመልክቶ በብሮድካስት ባለሥልጣንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፤ በብዙኃን መገናኛ አጠቃቀምና ድልድል አስመልክቶ በቀረበው ማብራሪያ ላይ ወደ ሥራ ሲገባ አሻሚ ትርጉም ፈጥረው ለአሠራር አስቸጋሪ ይሆናሉ ያሏቸውን አስተያየቶች ተሣታፊዎቹ አንሥተው ሁለቱም ተቋማት እንደየድርሻቸው የተሰጡት አስተያየቶቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍን አስመልክቶም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ማብራሪያ ሰጥተውበት ከተሣታፊዎቹ ሃሳብ የተሰበሰበ ሲሆን፤ በዋና ሰብሳቢዋ ብርቱካን አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። ሰብሳቢዋ አያይዘውም ለምርጫ ክርክር በሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የቀረቡ የክርክር ሃሳቦችን የይዘት ቅርጽ ላይ ያላቸውን አስተያየቶችና መሣተፍ የሚፈልጉባቸውን የክርክር ሃሳቦች እንዲመርጡ ቢጠየቁም እስካሁን የተወሠኑ ፓርቲዎች ብቻ እንዳስገቡ እንዲሁም የዕጩዎቻቸውን ዝርዝር ያላስገቡ ፓርቲዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ፓርቲዎቹ መረጃዎቻቸውን በተፈለገው ጊዜ ማስገባታቸው ለሥራው ሂደት አጋዥ ከመሆኑ አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያስገቡ አሳስበዋል።

 

Share this post