Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የመራጮች ምዝገባ ሂደት አፈጻጸምና አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሂደቶች እንዲሁም መጪ ሁነቶችን የተመለከተ ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የመራጮች ምዝገባ ሂደት አፈጻጸምና አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሂደቶችን እንዲሁም ቀጣይ የምርጫ ተግባራትን የተመለከተ ብዙኃን መገናኛ አካላት በተገኙበት ውይይት አካሂዷል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተከፈተው መድረክ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት፣ የሎጀስቲክ ማጓጓዝ፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደትና የተለያዩ ተግዳሮቶች ከነተሰጡባቸው መፍትሔዎች ጭምር ቀርበውበታል። በሎጀስቲክ ማጓጓዝ ወቅት የተፈጠሩ መስተጓጎሎች፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የተስተዋሉ የምርጫ ጣቢያዎች በጊዜ አለመከፈትና የተከፈቱት ሲሞሉም በአፋጣኝ ንዑስ ጣቢያዎችን ለመክፈት ከክልልና ከከተማ መስተዳደሮች ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለመስጠት እንደተሞከረ ሆኖም ግን በሚፈለገው ፍጥነት ቦታዎቹን ማግኘቱ ቀላል እንዳልነበረ ተገልጿል።

የመራጮች ምዝገባ ምርጫ አስፈጻሚዎች ክፍያ አፈጻጸም ረገድ የተስተዋሉ መስተጓጎሎች መንስዔዎቻቸውና የተወሰዱ ዕርምጃዎች በቦርዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሜላትወርቅ ኃይሉ አማካኝነት የቀረቡ ሲሆን፤ በኮንዶሚኒየም አካባቢዎች ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተገናኘ የተፈጠሩት ክፍተቶችና የተወሰዱ ዕርምጃዎች ደግሞ በኦፕሬሽን ክፍል ባልደረባ አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ተሣታፊዎቹ ቦርዱ የዳበረ ግኝቶችን ከተሰጡባቸው መፍትሄዎች ጭምር በዝርዝር ማቅረቡን ያደነቁ ሲሆን፤ ለተሰጡት መፍትሔዎችም አመስግነዋል። ያም ሆኖ አሁንም ድረስ በዕጩዎቻቸው ላይ ይደርስብናል ያሏቸውን መንገላታቶችና ማስፈራሪያዎች፤ በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ጭምር የበታች የመንግሥት መዋቅሮች ከምርጫ አስፈጻሚዎች ዐቅም በላይ በሆነ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ወኪሎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉባቸው ምርጫ ክልሎቹን በመጥቀስ ጭምር አቅርበዋል።

ዋና ሰብሳቢዋ የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሣኔን፣ ባልዳራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አካሄድኩት ያለውን ጥናትና ሌሎች የቀረቡ ጥያቄዎችን አስመልክቶ መልስ የሰጡ ሲሆን፤ ሰብሳቢዋ ምንም እንኳን ባልዳራስ ላደረገው ጥናት አድናቆታቸውን ቢገልጹም፤ ነገር ግን ጥናቱ ክፍተቶችን ሳይረፍድ በጊዜ ዕርማት በመስጠት ለውጥ ለማምጣት ያለመ ከሆነ ከሥር ከሥር ከፓርቲዎች ጋር እየተደረጉ በመጡት የምክክር መድረኮች ላይ አስተያየት በመስጠት እንዲታረሙ የሚደረግበትን አማራጭ መፈለግ የተሻለ እንደነበር ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የተባለው ጥናት የተደረገው ፓርቲው የፓርቲ ወኪል መታወቂያ ወስዶ ምርጫ ጣቢያዎችን የመጎብኘት እውቅና ባልወሰደበት ሁኔታ እንዲሁም ለዚህም ቦርዱ የሚታዩትን ክፍተቶች በአካልም ሆነ በጽሑፍ በመግለጽ አብረን መፍትሔ ማምጣት እንችላለን ብሎ በተለያዩ የምክክር መድረኮች ላይ ከተገለጸበት መንፈስ ውጪ እንደሆነ ገልጸው በተለይ የተዘጉ ምርጫ ጣቢያዎች የተባሉትን አስመልክቶ ቦርዱ የሰራቸው ስራዎች እና የተከፈቱ 47 አዳዲስ ጣቢያዎችን አስታውሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ ቅሬታዎች ካሉ መዝገብ ይፋ በሚሆንበት ወቅት ሚዲያዎች፣ የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ታዛቢ ሲቪል ማህበራት በመጎብኘት ችግር ካዩ በህጉ መሰረት እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሣኔ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎት ማራመጃ እንዳይሆን ለቀረበው ጥያቄ ዋና ሰብሳቢዋ ሲመልሱ፤ ሕዝበ ውሣኔ የሕዝብን ፍላጎት እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፍላጎት የማወቂያ መንገድ እንዳልሆነ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። የምርጫውን ሂደት ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ለተሰጡ አስተያየቶች ሰብሳቢዋ መልስ የሰጡ ሲሆን፤ አቤቱታዎች ከገዢው ፓርቲ ጭምር ለቦርዱ እንደሚደርሰውና ቦርዱ ማስረጃ የቀረበባቸውን አቤቱታዎች አፋጣኝ መልስ እንደሚሰጥ፤ ማስረጃ ያልቀረበባቸውን ደግሞ የክትትል ሥራ እንደሚሠራባቸው ተናግረዋል። ዋና ሰብሳቢዋ ከሁሉም አጋሮች ጋር በጋራ በምንወስዳቸው ሃላፊነቶች ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው የምርጫ ሂደት እንዲሁም ውጤት ማምጣት እንችላለን ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል።

የመራጮች ምዝገባ፣ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመትና ተያያዥ የኦፕሬሽን ሥራዎች የወሰዱት ተጨማሪ ጊዜ በመኖሩ፣ ለሎጀስቲክ ማጓጓዣም በቂ ጊዜ በማስፈለጉ፣ እንዲሁም በአንድ ምርጫ ጣቢያ ሦስት የነበሩትን የምርጫ አስፈፃሚዎች ቁጥር መጨመር የአፈጻጸሙን ሂደት የተሻለ ለማድረግ፤ የምርጫውን ድምፅ መስጫ ቀን ከሁለትና ከሦስት ሳምንት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም ማስፈለጉ በቦርዱ ሃሳብ ቀርቦበት መድርኩ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ፓለቲካ ፓርቲዎቹም እስካሁን ቦርዱ ደረጃ በደረጃ በየምክክር መድረኮች የምርጫውን ሂደት እያሳወቀ እንደመምጣቱ መጠን የምርጫው ቀን በተወሰሠነ ደረጃ ገፉ የመደረጉ ነገር ተገማች እንደነበር ተናግረዋል። በምርጫው ቀን መገፋት ድጋፋቸውን የሰጡት ፓርቲዎቹ ከግምት ውስጥ ቢገቡ ያሏቸውን አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን፤ በጽሑፍም ጭምር ገንቢ ሃሳባችን ለማጋራት ቦርዱ ክፍት እንደሆነ ከሰብሳቢዋ በኩል ተጠቅሷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ሀገር ዐቀፍ ምርጫው ከአዲስ አበባና ከድሬድዋ ከተማ መስተዳደሮች ምርጫዎች ጋር በተመሳሳይ ቀን ይደረግ የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው፤ ቦርዱ ምርጫው ላይ ምንም ዓይነት የተአማኒነት ጥቁር አሻራ መጣል ስለማይፈልግ፤ የሁለቱ ከተማ መስተዳደሮችን ምርጫ ከሀገር ዐቀፉ ምርጫ ጋር በተመሳሳይ ቀን መደረጉ የሚፈጥረውን የአፈጻጸም ክብደት ለማስቀረት ሊረዳ የሚችል አዲስ ዕቅድ በመንደፍና ለአስፈጻሚዎችም ልዩ ሥልጠና በመስጠት በተመሳሳይ ቀን እንዲደረግ ሲል መወሰኑም በእለቱ ተጠቅሶ ከፓርቲዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።

 

Share this post