የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልጽ የሚደረግበት ሂደት
የመራጮች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ተግባራዊ ከሚሆኑ ዋና ዋና የምርጫ ተግባራት አንዱ የመራጮች መዝገብን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች መዝገብ ይፋ የማድረግን ሂደት ከቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2013 - ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ያከናውናል።
በዚህም ወቅት ምርጫ ጣቢያዎች ክፍት ሆነው መዝገቡ ለህዝብ ይፋ የሚሆን ሲሆን በመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች መረጃቸውን ለማጣራት፣ መታወቂያ የወሰዱ ወኪሎች ያሏቸው ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች እና ታዛቢዎች ሂደቱን ሊያዩት ይችላሉ። ይፋ የማድረግ ሂደቱም እንደሚከተለው ሲሆን በዚህ ሂደት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች ወይም አስተያየቶች ካሉ ለማሻሻል ይረዳን ዘንድ በነጻ የስልክ መስመራችን 778 በመደወል እንዲያሳውቁን ቦርዱ በአክብሮት ይጠይቃል።
የመራጮችን መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የማድረግ ሂደቶች
1. የመራጮች ምዝገባ እንደተጠናቀቀ የመራጮች መዝገብ በምርጫ ጣቢያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለተከታታይ 10 ቀናት ይፋ ሆኖ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው ይደረጋል፡፡
2. የመራጮችን መዝገብ ለመመልከት የምትቀርብ/የሚቀርብ ሰው የመራጭነት ምዝገባ ካርዷን/ካርዱን እና የማንነት መታወቂያ ካርድ ወይም ማንነቱዋን/ማንነቱን የሚያውቅ ምስክር ማቅረብ አለባት/አለበት::
3. የመራጮች መዝገብ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው የሚደረገው በሚከተለው አሰራር ይሆናል፤
ሀ) የመራጮችን መዝገብ ህዝቡ በግልፅ እንዲያይ የሚያደርጉት በምርጫ ጣቢያው የመዝገብ ሹም ሆነው የተመደቡት የምርጫ አስፈፃሚ አባላት ናቸው::
ለ) የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ መዝገቡን ለመመልከት የሚፈልጉትን ሰዎች እንዳመጣጣቸው ተራ በተራ ወደ መዝገቡ እየቀረቡ እንዲመለከቱ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ታመቻቻለች/ያመቻቻል፣ ታስፈፅማለች/ያስፈጽማል፡፡
ሐ) የመራጮችን መዝገብ መመልከት የምትፈልግ/የሚፈልግ ሰው ወደመዝገብ ሹም በመቅረብ የምትፈልገውን/የሚፈልገውን መረጃ ከመዝገቡ ለማየት የመዝገብ ሹሟን/ሹሙን ትጠይቃለች፡፡ የመዝገብ ሹሟም/ሹሙም የተጠየቀውን መረጃ ለሚመለከታት/ለሚመለከተው ሰው መዝገቡን በመግለፅ ታሳያለች/ያሳያል፡፡
መ) የመራጮችን መዝገብ የምትመለከት/የሚመለከት ሰው በመዝገብ ሹሟ/ሹሙ አማካኝነት የምትፈልገው/የሚፈልገውን መረጃ ያለበትን ገጽ /ገፆች/ በዓይን ከማየት ወይም መረጃው ሲነበብላት/ሲነበብለት ከማዳመጥና ማስታወሻ ከመያዝ ውጪ በእጇ/በእጁ መንካት፣ መዝገቡ ላይ መፃፍ፣ ምልክት ማድረግ፣ ወይም ፎቶግራፍ ማንሳት የተከለከለ ነው::
4. የመራጮች መዝገብ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው ሲደረግ የምርጫ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የግል እጩ ወኪሎች እና የምርጫ አስፈፃሚዎች ሊገኙ ይችላሉ፡፡
5. የመራጮች መዝገብ ከላይ በንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት ይፋ ወጥቶ ቅዳሜ እና እሁድን እንዲሁም በዓላትን ጨምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት ህዝቡ በግልፅ እንዲያየው የሚደረገው በየዕለቱ በመንግሥት የሥራ ሰዓት ይሆናል::
6. የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የሚሆንባቸው ቀናት ሲጠናቀቅ ስለሂደቱ የቀረበ አቤቱታ እና የተሰጠ መልስ ካለ እና ስለተሰጠው መልስ በአጭሩ እንዲሁም መዝገቡ ለሕዝብ ግልፅ በሆነባቸው ቀናት የተገኙ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የግል እጩ ወኪሎችን የሚመለከቱ መረጃዎች ተፅፈው በሰነድነት ይያዛሉ።
7. እውቅና መታወቂያ ያላቸው የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የእውቅና መታወቂያ ያላቸው የሚዲያ ባለሞያዎች እና ታዛቢዎች ይፋ የሆነውን መዝገብ መመልከትም ሆነ ይፋ የማድረግ ሂደቱን መከታተል ይችላሉ።
በመራጭ አመዘጋገብ ሂደት የተፈፀመ ስህተት የሚስተካከልበት አግባብ
በመራጭነት የተመዘገበች/የተመዘገበ ሰው የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ በሆነበት ጊዜ የግል መረጃዋን/መረጃውን በተመለከተ ስህተት አለ የሚል ቅሬታ ካላት/ካለው እንዲስተካከልላት/እንዲስተካከልለት ለምርጫ ጣቢያው ማመልከት ትችላለች/ይችላል፡፡ ምርጫ አስፈጻሚውም ሰነዶችን በማየት በህጉ መሰረት ማስተካከያ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ