Skip to main content

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር በቦርዱ የክልል ጽ/ቤቶች የሚሰሩ የተባበሩት መንግስታት በጎ ፍቃደኞች ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳና የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ በተገኙበት ለሁለት ቀናት የሚቆየውን የተባበሩት መንግሥታት የበጎ ፍቃደኞች ሥልጠና አስጀምረዋል። የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ላይ የሚኖረውን የሥራ ሂደት ቀልጣፋና ዘመናዊ አፈጻጸም እንዲኖረው ለማስቻል ታስቦ ከተባበሩት መንግስታት በጎ ፍቃደኝነት ተቋም ጋር በመተባበር በጎ ፍቃደኞች የተመለመሉ ሲሆን በዛሬው እለት የተዘጋጀላቸው የስልጠና መርሃ ግብርን የቦርዱ ሰብሳቢ ከፍተውታል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫ ከዋና አገራዊ ሁነቶች አንዱ መሆኑን አውስተው፤ ለዚህም የጠንካራ ተቋም መኖር ወሳኝ እንደሆነና ተቋምንም ጠንካራ ለማድረግ በብቁ ባለሞያዎች ማደራጀት ትልቁ ዐቅም እንደሆነ ገልጸዋል። ዛሬ የተጀመረው ሥልጠናም በ6ተኛ ሀገራዊ ምርጫ የሁሉም ማኅበረሰብ ክፍሎች ድምፅ ዋጋ እንዲኖረው ለማስቻል ለምናደርገው ከፍተኛ ጥረት ያለው ሚና ትልቅ ነው ብለዋል። ታማኝነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ገለልተኛ በመሆን ብቻ ሣይሆን ተቋማዊ ዐቅም በመፍጠር ጭምር ነው ያሉት ብርቱካን፤ ዐቅም ለመፍጠር ቦርዱ ለሚያደርገው ጥረት የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት እያደረገ ያለውን እገዛ አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በጎ ፍቃደኞች አስተባባሪ የሆኑት ሰላማዊት ፅጌ በበኩላቸው፤ የበጎ ፍቃደኞች አገልግሎት ለመልካም ለውጦች፣ ለድኅነት ቅነሳ፣ ለሥርዓተ-ፆታ ዕኩልነት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለዲሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው፤ ዛሬ የተጀመረው ሥልጠና ዋና ዐላማም እሱ እንደሆነ አብራርተዋል።

ስልጠናውም የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሠሌዳና የአፈጻጸም ሂደት፣ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት፣ ምርጫና ሥርዓተ-ፆታ፣ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሂደት፣ የምርጫ ጣቢያዎችና የድምፅ ቆጠራ ሥርዓት ሂደት እንዲሁም IT ሥልጠናው ትኩረት ከሚያደርግባቸው አጀንዳዎች ውስጥ ተካተውበታል።

NEBE/UNV

 

Share this post