መልስ - ለአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ከተማ መስተዳድሮች ምክር ቤቶች የድምፅ መስጫ ቀን ከአገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተመሳሳይ አለመሆኑን ቦርዱ አሳውቋል፡፡ ይህም የሆነው ግንቦት 28 ቀን 2013 የሚካሄደው ምርጫ የፌዴራል መቀመጫ የሚመረጥበት የምርጫ ክልል (constituency) እና የአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተሞች መስተዳደር መቀመጫዎች የሚመረጡት የምርጫ ክልል (constituency) በመለያየቱ ነው፡፡ የከተማ መስተዳድሮች/ ክልሎች የምርጫ ክልሎቻቸው የሚወስኑት በራሳቸው ሲሆን ቦርዱ የክልል/የከተማ መስተዳድሮች ምርጫን የሚያስፈጽመው ክልሎች/ከተማ መስተዳድሮች በወሰኑት የምርጫ ክልል መሰረት ነው።  ለምሳሌ በምርጫ 97 የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መቀመጫ የሚመረጥበት የምርጫ ክልል እና ከከተማው ለተወካዮች ምክርቤት ተወካዮች የሚመረጡበት የምርጫ ክልል ተመሳሳይ የነበረ ሲሆን ቆጠራውም በተመሳሳይ የሚቆጠር በመሆኑ ምርጫ አስፈጻሚዎች ውጤት ሲያሳውቁ ለተመሳሳይ የምርጫ ክልል ሪፓርት ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከምርጫ 97 በኋላ 2000 . በተካሄደው የከተማው መስተዳድር መቀመጫ ምርጫ የከተማ መስተዳድሩ የምርጫ ክልሎቹን በመቀየር ክፍለከተሞችን እንደምርጫ ክልል አዋቅሮ ምርጫዎቹም በዚያ መሰረት ሲከናወኑ ቆይተዋል። ከዚያ በኋላ የነበሩት ምርጫዎችም የከተማ መስተዳድሩ ምርጫ ከፌደራል ምርጫ ጊዜ በተለየ ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል። የድሬደዋ ከተማ መስተዳድርም ከፌደራል መቀመጫ (2 ብቻ) በተለየ በመስተዳድሩ ስር ያሉትን 47 ቀበሌዎች እንደመስተዳድሩ የምርጫ ክልል ስለሚጠቀምባቸው አንድ ሰው ድምጽ ሲሰጥ ለፌዴራል መቀመጫ ድምጽ የሚሰጥበት እና ለመስተዳድሩ ድምጽ የሚሰጥበት የምርጫ ክልል ይለያያል። ይህም ውጤት ቆጠራን በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል። እንደሚታወሰውም የድሬደዋ ከተማ ምርጫም ከፌደራሉ በተለየ ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል።

1