Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የብሔረሰብ ጥናት ኢንስትቲዩት መዛግብትን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ አስረክቧል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 12 ቀን 2013 ዓ.ም የብሔረሰብ ጥናት ኢንስትቲዩት መዛግብትን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ አስረክቧል። ቦርዱ በቀድሞው መንግሥት አስተዳደር በመጋቢት 1975 ዓ.ም የተቋቋመውን የብሔረሰቦችን ጉዳይ የሚያጠናውን ተቋም ሠነዶች ወርሶ እንደቆየ የሚታወቅ ሲሆን፤ በወቅቱ በተቋሙ የተሠሩ ጥናቶች አምስት የተለያዩ ዘርፎች ማለትም

• የታሪክ፣ የባሕልና የቋንቋ ጥናት
• የማኅበራዊ ዘርፍ
• የአስተዳደር ጥናት ቡድን
• የኢኮኖሚ ጥናት ቡድን እና
• የሕገ-መንግሥት ጥናት ቡድን ያካተተ ነበር።

ጥናቱን በሁሉም ዘርፎች ላይ አምስት ምሁራን በዋናነት ሲመሩት በሥራቸው ከአምስት በላይ በከፍተኛ ደረጃ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ወጣት ተመራማሪዎች ተሳትፈውበታል። ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን መዛግብት ለኤጀንሲው ለማስረከብ ሲወስን በጉዳዩ ላይ የበለጠ መረዳትና ምርምር ለማድረግ ለሚሹ መዛግብቱን በቀላሉ ሊያገኛቸው በሚችሉበት ቦታ ማስቀመጡ ያለውን ጠቃሜታ በመረዳት ነው። የመዛግብቱን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳና የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ይኮኖ አምላክ መዝገቡ እንዲሁም በወቅቱ ጥናቱን ያካሄዱት ምሁራንና የብዙኃን መገናኛ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ በቦርዱ ሰብሳቢ በብርቱካን ሚደቅሳና በዳይሬክተር ይኮኖ አምላክ መዝገቡ የመክፈቻ ንግግር ተከፍቶ አጥኚ ምሁራኑ ሀሳባቸውን እነዲያካፍሉ የተደረገበተ ሲሆን፤ መዛግብቱን ለተጋባዥ እንግዶችና ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት በማድረግ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Share this post