የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲዎች ምዝገባ ጥያቄዎች ዙሪያ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ
ታኅሣሥ 16 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእውቅና ጥያቄ እና፣ የፓርቲ መለያ ሰንደቅ ዓላማ የማጸደቅ ጥያቄን ያቀረቡ ፓርቲዎችን ጉዳይ አይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል በዚህም መሰረት፦
1.የኢህአዴግ አባል የነበሩ ሦስት ፓርቲዎች እና ሌሎች አምስት ፓርቲዎች በጋራ ራሳቸውን በማክሰም ብልጽግና ፓርቲን መመሥረታቸውን በማሳወቅ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጣቸው ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሁፍ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረቡ ሲሆን ቦርዱም ጥያቄያቸውን በፓለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ አዋጅ 1162/2011 መሠረት መርምሮ ውሳኔውን ሰጥቷል። በዚህም መሠረት ቦርዱ የእውቅና ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ በተጨማሪ መሟላት ያለባቸውን ሰነዶች በታኅሣሥ 01 ቀን 2012 ዓ.ም. በመጠየቅ በጥያቄውም መሠረት ታኅሣሥ 06 ቀን 2012 ዓ.ም. የጥያቄዎቹ ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሟልተው መቅረባቸውን በማረጋገጡ ብልጽግና ፓርቲን ለመመሥረት፦
1. የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣
2. የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣
3. የሃረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣
4. አማራ ዴሞክራያዊ ፓርቲ ( አዴፓ) ፣
5. የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ)፣
6. የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ፣
7. የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ፓርቲ (ጋሕአዴን)፣
8. የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ( ቤጉሕዴፓ)።
በተናጠል በጠቅላላ ጉባኤያቸው ውሳኔ መሰረት አድርገው ውህደቱን ለመቀላቀልና ፓርቲያቸውን ለማክሰም የወሰኑት ውሳኔዎች እንዲሁም ውህደቱን ለመመስረት ያደረጉትን ስምምነት በሙሉ ህጉን ተከትሎ የተፈጸመ በመሆኑ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ተሰርዘው ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ወስኗል።
በዚህም መሰረት ውህዱ ፓርቲ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 92/2 መሠረት በተመዘገበ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ውህደቱ ያስገኘውን ሃብትና ንብረት እና እዳ የሚያሳይ የሂሳብ ሪፓርት ለቦርዱ እንዲያቀርብ በውሳኔው ውስጥ ተካቷል።
2. የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ በምዝገባ ወቅት ያቀረበው ሰንደቅ ዓላማ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ይመሳሰላል በሚል በቦርዱ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይመሳሰል በመግለጽ ልዮነቱን አብራርቶ ቦርዱ እንዲቀበለው ጥያቄ አቅርቧል። ቦርዱ በሁለቱ ሰንደቅ አላማዎች መካከል አለ የተባለውን ልዩነት መርምሮ የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ የጠቀሳቸው ልዩነቶች ለማስተዋል የሚያስቸግሩ በመሆናቸው እና ድምፅ ሰጭዎችን የሚያምታቱ ሆነው ስለሚገኙ ሰንደቅ አላማውን ቀይሮ በማቅረብ ምዝገባውን እንዲያጠናቅቅ ውሳኔ ሰጥቷል።
3. እናት ፓርቲ በሚል አገር አቀፍ ፓርቲ ለማቋቋም በሂደት ላይ ያለ ፓርቲ በአዋጅ 1162/ 2011 መሠረት ጊዜያዊ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን ጊዜያዊ ሰርተፍኬት መውሰጃ መስፈርት በማሟላቱ እናት ፓርቲ የጊዜያዊ እውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ቦርዱ ወስኗል።