Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዮ አገር አቀፍ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ህትመትና የቁሳቁሶች ግዥ ጀመረ

ታኅሣሥ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን የመራጮች ምዝገባን ዘመናዊ እና ተአማኒ የሚያደርግ የህትመት ሥራ እንዲጀመር በትላንትናው  ዕለት በዱባይ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የዚህ የህትመት ውል ዓላማ የምርጫው ሂደት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እና አዲሱ የምርጫ ህግ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች ያሟላ እንዲሆን፣ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶችን ለመቀነስና እና ማጭበርበርን ለማስወገድ የሚረዳ እንዲሆን እንዲሁም ለምርጫ አስፈጻሚዎች ለመረዳትና ለማስፈጸም ቀላል እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡

ይህ የህትመት ሥራ ከዚህ በፊት ከነበሩትና አገር ውስጥ ከሚደረጉ ህትመቶች የተለየ ሲሆን፦
1. የመራጮች መመዝገቢያ መዝገቡም ሆነ የምዝገባ ማረጋገጫ ካርድ የራሳቸው የደህንነት ማረጋገጫ (security feature) ያላቸውና ሊጭበረበሩ እና ሊባዙ የማይችሉ መሆናቸው፣
2. የመራጮች ካርድ ቀሪ ያለው ሆኖ የሚዘጋጅና መራጮች ጋር ያለው ካርድ ቀሪ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር የሚቀር መሆኑ በምዝገባ ወቅት ሊፈጠር የሚችል ማጭበርበርን የሚያስቀር መሆኑ፣
3. እያንዳንዱ መራጭ በመራጮች ካርዱ አማካኝነት የራሱ የሆነ ልዩ መለያ ቁጥር ያለው መሆኑ ሲሆን ሁሉም ሰነዶች በአምስት ቋንቋ ማለትም፣ በአማርኛ፣ በአማርኛ/ትግርኛ፣ በአማርኛ/አፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ/ሶማሊኛ እንዲሁም በአማርኛ/ አፋርኛ የሚታተሙ ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ህገ ወጥ የሆነ የምርጫ እቃዎች አግባብ ባልሆነ እጅ እንዳይወድቁ እቃዎቹ የሚታሸጉበት ልዩ ቁሳቁስ ለመራጮች ምዝገባም ሆነ ለድምፅ መስጫ የሚውል ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ የህትመት ሂደቱ ጋር አብሮ የሚከናወነው ግዥ ጥቅል የሆነ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ፣ የማጭበርበር ሙከራ ካለ ሊያጋልጥ የሚችል የፕላስቲክ ቦርሳ (temper evident bags) እና የአጠቃቀም ስልጠናን የሚያካትት ይሆናል፡፡
ይህንን ህትመት የሚያከናውነው ድርጅት ለኬንያ፣ ለኡጋንዳ፣ ለማላዊና ለዛምቢያ የምርጫ ሰነዶችን በማተም የሚታወቅና የምርጫ ሥራዎችን በልዮ ሁኔታ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡

Share this post