Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ አመራር ውዝግብ ዙሪያ ሲቀርብለት ለቆየው አቤቱታ ውሳኔ ሰጠ

ታኅሣሥ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.   

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ ኢዴፓ/ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቆየውን የፓርቲው አመራር ምርጫ እና ተያያዥ ውዝግብ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ኢዴፓ (እነ አቶ አዳነ ታደሰ) በ25/02/2012 በተጻፈ ደብዳቤ የኢዴፓ አመራር ምርጫ እና የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባን አስመልክቶ ለቦርዱ ዝርዝር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን አቤቱታውም፣ ኢዴፓ ሐምሌ 06 ቀን 2011 ዓ.ም. አስቸኳይ ፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባ ማድረጉን በዚህ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን እና ያሳለፈው ውሳኔ በቦርዱ እውቅና እንዲያገኝ ቢጠይቅም በቦርዱ እውቅና እንዳላገኘ በዚህም መሠረት የእርምት እርምጃ ወስዶ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በድጋሚ ልዩ አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉን፣ ስብሰባው የተጠራው በምክር ቤቱ አባላት ፒቲሽን መሆኑን፣ የስብሰባው ቀን ሰዓት ሥራ አስፈጻሚው በወሰነው መሠረት ማካሄዱን በዚህ ምክር ቤቱ ሁለተኛ ጉባኤ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት ተገኝተው ስብሰባውን መታዘባቸውን ከዚሁ ጋር በማያያዝም በቦርዱ የተሰጠው መመሪያ መሠረት በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ይህንን የእርምት እርምጃ መውሰዱን ስለዚህም በዚህ ጉባኤ የተሰጡ ውሳኔዎች እውቅና አግኝተው ተፈጻሚ እንዲሆኑ ተገቢውን ሁሉ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

በዚህም መሠረት ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን ሰነዶች፣ መተዳደሪያ ደንቡን እንዲሁም ቃለጉባኤዎቹን ከመረመረ በኋላ ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ይህ አስቸኳይ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ በፓርቲው ህገ ደንብ እንዲሁም ኮረም ሞልቶ የተከናወነ ስብሰባ መሆኑን ቦርዱ ተገንዝቧል፡፡
በመሆኑም ቦርዱ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ የተወሰኑት ማለትም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ፣ የጠቅላላ ጉባኤ ቀን እና የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ምርጫ፣ አራት አባላቱን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ከብሔራዊ ምክር ቤት ማሰናበቱ እና ሌሎች ቃለ ጉባኤው ላይ የሚገኙ ውሳኔዎች ህጋዊ ናቸው ብሎ በመወሰን ለሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን የትብብር ደብዳቤ በመጻፍ ማሳወቁን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

 

 

Share this post