Skip to main content

ቦርዱ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ ፍቃድ የሰጣቸው የሲቪል ማኅበረስብ ድርጅቶች ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የመራጮች ትምህርት ሰጡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ የማሰተማሪያ ፍቃድ የሰጣቸው የሲቪል ማኅበረስብ ድርጅትች በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በሲዳማ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ለሚገኙ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የመራጮች ትምህርት ሰጡ::

ከቦርዱ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል እንዲሁም ከቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር በክልሎች እና በከተማ መስተዳድሮች በገጽ ለገጽ፣ በጎዳና ላይ ቅሰቀሳ፣ በራሪ ወረቀቶችን በመጠቀም፣ በተጨማሪም በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች እንዲሁም የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማኅበረሰቡ በማድረስ የመራጮች ምዝገባን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ሰጥተዋል። በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ማኅበራቱ በቀጣይም የድምፅ መስጠት ሂደቱ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን የሚሠሩ ይሆናል።

በምርጫ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና በምርጫ ሥነ ምግባር ዐዋጅ ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 124 (2)” ላይ “ቦርዱ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዲችሉ ሕጋዊ ሰውነት ላላቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የትምህርት ተቋማት፤ የማስተማር ፈቃድ ይሰጣል” በሚል የተደነገገ ሲሆን፤ በዚህም መሠረት በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 169 የሲቪል ማኅበረስብ ድርጅቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማስተማር ፍቀድ ሰጥቶ ወደ ሥራ መሠማራታቸው ይታወቃል፡፡

Share this post