ቦርዱ በክርክር ክኅሎት ልምምድ ምንነት እና አተጋባበር ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቸን ያሣተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በፓለቲካ ፖርቲዎች መካከል የሚካሄደው የፖሊሲ አማራጮ ክርክርን ታሳቢ ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን ባሣተፈ መልኩ በትላንትናው ዕለት ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. አካሄደ። ፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይንሳዊ መንገድን ተከትለው ለመራጩ ሕዝብ ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራሞቻቸውን እንዴት ባለ ሁኔታ ማቅረብ እንዳለባቸው ግንዛቤ ማስጨበጥ ዐላማው ያደረገውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም መራጩ ሕዝብ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ እንዲወሥንና ድምፅ እንዲሰጥ ለማስቻል የመራጮች ትምህርትና የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ፖሊሲና ፕሮግራማቸውን የተመለከቱ ክርክሮችም እንዲሁ ወሣኝነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር ክኅሎታቸውን መዳበር የሕዝብ ተሣትፎን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለውና የዲሞክራሲ ሂደቱን እንደሚያጠናክር፤ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚመሳሰሉበትንና የሚለይበትን አጀንዳዎች ለማየት ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ቦርዱ ቀደም ሲል ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የክኅሎት ማዳበሪያ ሥልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን፤ ከነዚኽም ውስጥ “ሴት እና አካል ጉዳተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ፖለቲካዊ ተሣትፎና ተግዳሮቶች”፣ “የፖለቲካ ፓርቲዎችን የውስጥ አለመግባባት አፈታት ሥርዓታቸውን ለማጎልበት የሚያግዝ የዐቅም ግንባታ” እንዲሁም “የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳና የሕዝብ ግንኙነት ክኅሎት” የተመለከቱ ሥልጠናዎች ተጠቃሽ ናቸው።






