የቦርዱ ውጤታማ የፕሮግራም በጀት አተገባበር እንዲጠናከር ለቦርዱ ኃላፊዎች የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ሥራ ክፍሎቹ አማካኝነት ቦርዱ የተቋቋመለትን ዐላማ በብቃት መፈጸም የሚያስችለውን ሙያዊ ሥልጠና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሲያሰጥ ቆይቷል። ከዚኽም ጋር ተያይዞ የቦርዱን ስትራቴጂክ ዕቅድ ከመንግሥት የፕሮግራም በጀት ማዕቀፍ ጋር አቀናጅቶ የሚሠራበትን ውጤታማ የአሠራር ሥርዓት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል፤ በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤትና በክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹ ለሚሠሩ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች የአራት ቀናት የዐቅም ግንባታ ሥልጠና በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዮት ባለሞያዎች አማካኝነት ሰጠ፡፡
ከግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በተሠጠው ሥልጠና ላይ ትኩረት ከተደረገባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ውስጥ የመንግሥት የፕሮግራም በጀት መርኆችን፣ የበጀት ዝግጅት ክኅሎትን፣ የፕሮግራም በጀት አሠራር ምንነትን፣ በጀትን በጥራትና በቅልጥፍና ለማዘጋጀት የሚረዱ ቴክኒኮችን፣ እንዲሁም በጀትን ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ የሚረደ የክትትል የአሠራር ሥርዓትን የተመለከቱ ይጠቀሳሉ።
በቦርዱ የፋይናንስ እና በጀት ሥራ ክፍል አስተባባሪነት በተሰጠው ሥልጠና ላይ ከፕሮግራም በጀት የአሠራር ሥርዓት በተጨማሪ በፋይናንስ ሠነዶችና ተያያዥ መረጃዎች አያያዝን በተመለከተ ለቦርዱ የፋይናንስና በጀት፣ የግዢ፣ የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት የሥራ ክፍል ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናው በሁሉም የቦርዱ ሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች መካከል የፕሮግራም በጀት ዓላማና ግቦችን በተመለከተ የጋራ መረዳትን በመፈጠር፤ የፋይናንስና ሌሎች ተያያዥ ሠነዶች ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲደራጁና የፋይናንስ ሥራውን የሚደግፉ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት እንዲዘረጋና እንዲጠናከር፤ በውጤቱም የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር ያስችላል ተብሎ ይታመናል።










