የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የኅትመት ውጤቶችን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሠራጨ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርትን እንዲሁም የመራጮች መረጃን ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ይገኛል። ቦርዱ ትምህርቱን ተደራሽ ከሚያደርግባቸው ዘዴዎች አንዱ የተለያዩ የኅትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት ለተለያዩ ተቋማትና ቤተ-መጽሓፍት ተደራሽ ማድረግ ነው።
ከዚህም ጋር በተያያዘ የቦርድ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ሥራ ክፍል ከቦርዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት በአምስት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ማለትም፤ ‘የምርጫ ሒደት’፣ ‘ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ ‘ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች’ ፣’ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ እንዲሁም ‘ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት’ የሚሉ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና በምርጫ ሂደት ዙሪያ የሚያተኩሩ 2,500 ብሮሸሮች እንዲሁም ‘ምርጫ በኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ የተዘጋጁ 2,000 መጽሔቶች በክልሉ 12 ዞኖች ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች አሠራጭቷል። እነኚሁ ብሮሸሮች ለዓይነ ሥውራንም በብሬል መልኩ ተዘጋጅተው ተሠራጭተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቦርዱ 150 ‘የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011’ ለየትምህርት ቤቶቹ እንዲዳረስ አድርጓል። የኅትመት ውጤቶቹን የተረከቡት የየት/ቤቶቹ ርዕሳነ-መምህራን እነዚህን መሰል የኅትመት ውጤቶችን በት/ቤቶቹ ቤተ-መጽሓፍት መገኘታቸው ተማሪዎቹ ስለ-ምርጫ ሂደት እንዲሁም ስለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተሣትፎ ጠቀሜታ እንዲረዱ ከማስቻሉም ባሻገር፤ ተማሪዎቹ ካሏቸው ቤተሰባዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮች አኳያ መልዕክቱን ብዛት ላለው የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።




