የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአሶሳ ከተማ የወጣቶች ክርክር መድረክ አዘጋጀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል በዴሞክራሲ ሥርዓት፣ የምርጫ ሂደት እንዲሁም ፖለቲካዊ እና ማኀበራዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አካታች በሆነ መልኩ ለዜጎች ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ቦርዱ በሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል በኩል "ኤሌክቶራል አክተርስ ሰፖርት ቲም" (EAST) ከተሰኘ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር ኅዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ የተወጣጡ ተማሪዎችን ያሳተፈ የክርክር መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን ቦርዱ ይህን መሰል የወጣቶች የክርክር መድረክ ሲያዘጋጅ ለ12ኛ ጊዜ ነው።
በእለቱ ከተከራካሪ ቡድኖች በተጨማሪ፣ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እና መምህራን፣ የሚዲያ አካላት፣ የቦርዱ የሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የዩኒቨርስቲው ማኀበረሰቦች የክርክሩን መርሀ ግብር ታድመዋል። የክርክሩ መርሀ ግብር በሁለት የመከራከሪያ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ "ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው? ወይስ አይደለም?" በሚል የመጀመሪያው የክርክር ክፍለ ጊዜ የተከናወነ ሲሆን፣ በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ደግሞ "የኢትዮጵያ ምሑራን የዴሞክራሲ ልምምድ ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋን የሚሰጥ ነው? ወይስ አይደለም?" በሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ዙሪያ ተከናውኗል።
አካታችነትን መሠረት በማድረግ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እንዲሁም ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መረጃ እንዲኖረው የሚሠራው የቦርዱ የሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል፣ ይህን መሰል አሳታፊ ሥራዎችን በመሥራት እንደሚቀጥል ተገልጻል። በዚህም ዜጎች፣ በተለይም ወጣቶች መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዕውቀትን ከማግኘት ባሻገር፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሀሳብ ልዩነቶችን ማስተናገድ እንዲሁም ሀገራዊ የሆኑ ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሄ ሀሳቦችን በጋራ የመጠቆም ልምዳቸውን ለማዳበር ዕድል እንደሚያገኙ ይታመናል።