Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወጣቶች የክርክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ አዘጋጀ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና የምርጫ ሂደት ዙሪያ ሁሉን ዜጎች አካታች የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየተገበረ ይገኛል። በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከኤሌክቶራል አክተርስ ስፖርት ቲም (EAST) ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር ጥቅምት15 ቀን 2017 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ አሊያንስ ኮሌጅ የወጣቶች የክርክር መድረክ አካሒዷል። የክርክሩ ተሳታፊዎች ከኮሌጁ የተውጣጡ ተማሪዎችና የአከባቢው ወጣቶች ሲሆኑ በሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም፡ "የማህበራዊ ሚዲያ ለወጣቶች ዴሞክራሲያዊ ልምምድ ያለው አስተዋፆ አዎንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ ?" እንዲሁም "ወጣቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው ወይስ አይደለም?" በሚሉ አርዕስቶች ላይ በሁለት ቡድን በመከፈል ተሟግተዋል ። በመድረኩ የኤሌክቶራል አክተርስ ስፖርት ቲም ዋና ስራ አስኪያጅን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ባለሙያዎች፣ የአሊያንስ ኮሌጅ አስተዳደር እና ተማሪዎች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የአከባቢው ወጣቶች ፕሮግራሙ ላይ ታድመዋል። ይህን መሰል መድረክ መዘጋጀቱ በተለይ ወጣቶች በሀገራችን አብዛኛውን ቁጥር እንደመወከላቸው መጠን ስለ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸው ግንዛቤን እንዲጨብጡ እና ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያበረታታ በመሆኑ ለወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

Share this post