በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት የተቋቋመ ገለልተኛ ህገ መንግሥታዊ ተቋም ነው። ቦርዱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የፌደራል እና የክልል ጽህፈት ቤቶችን ያደራጀ ሲሆን በሁሉም ክልልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ቢሮዎች አሉት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስት አገራዊ ምርጫ ያስፈጸመ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ሁለት የአካባቢ ምርጫ፣ እና ስድስት ሕዝበ ውሳኔዎችን አደራጅቷል።

ቦርዱ እንደ አዲስ ራሱን ማዋቀር ከጀመረበት ከታህሣሥ ወር 2011 ዓ.ም. አንስቶ አዲስ የድጋሚ ማቋቋሚያ አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን ከዚህ በፊት ከነበረው አደረጃጀት በተለየ አምስት የሙሉ ጊዜ የቦርድ አባላት እንዲኖሩት ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የቦርዱ ጽህፈት ቤት በቦርዱ በራሱ የሚደራጅ ሲሆን የአንድ አባል የሥራ ዘመን ስድስት ዓመት ነው። በአዋጅ 1133/2011 መሠረት ለቦርዱ የተሰጡ ሥልጣንና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።

የቦርዱ ሥልጣንና ተግባራት

1.  በህገ መንግሥቱ እና በምርጫ ህግ መሠረት የሚካሄድ ማንኛውም ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት ማስፈፀም፤
2.  የመራጮችን ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት፤ መከታተልና መቆጣጠር፤
3.  የፖለቲካ ድርጅቶችን መመዝገብ፣ በህጉ መሠረት መከታተልና መቆጣጠር፤
4.  የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበትን መስፈርት ማውጣትና በመስፈርቱ መሠረት ድጎማውን ማከፋፈል፤
5.  በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መወሰን፤
6.  የምርጫ ክልሎችን አከላለል በተመለከተ ጥናት አድርጎ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ፤
7.  ለምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ መስጠት፣ መከታተልና መቆጣጠር፤
8.  የቦርዱን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በሁሉም ክልሎችና ከዚያ በታች ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ማደራጀት፤
9.  በየደረጃው እና በየጊዜው የሚካሄዱ ምርጫዎች ነፃ እና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድበትን ሁኔታ የማመቻቸትና የማረጋገጥ፤
10. ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች የማዘጋጀትና ማሰራጨት፤
11. በዚህ ህግና በሌሎች ህጎች የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን ማውጣት፤
12. ምርጫ አስፈፃሚዎችን ገለልተኝነትና ነፃነት የማረጋገጥ እንዲሁም በምርጫ አስፈጻሚነታቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው ተጽህኖ የመከላከል፤
13. ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የምርጫ ጣቢያዎችን ቁጥር መወሰን፤
14. ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያዎችን በመላው ሀገሪቱ ማደራጀት፤
15. ገለልተኛ፣ ብቃትና የሕዝብ ታአማኒነት ያላቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች መመልመልና ማሰልጠን፤
16. ከምርጫና ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማጠናከር፣ የምርጫ ህጎችንና አፈጻጸምን በመገምገም ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮችን   ለይቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ፤
17. የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክን ማስተባበር፤
18. የምርጫው ውጤቶችን ማረጋገጥና ይፋ ማድረግ፤
19. በምርጫ ሂደት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ መፍትሄ መስጠት፤
20. በምርጫ ሂደት የምርጫ ውጤትን የሚያዛንፍ የህግ ጥሰት ተከስቶአል ብሎ ሲያምን ውጤቱን መሰረዝና ድጋሚ ምርጫ ማካሄድ እንዲሁም በምርጫ ሂደት የተፈጸመ የህግ መጣስ፣ ማጭበርበር ወይም የሰላምና ፀጥታ ማደፍረስ ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ፤
21. በጀት አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ፣ ማጸደቅና በሥራ ላይ ማዋል፤
22. በየደረጃው የሚካሄዱ ምርጫዎችን መርሀግብር ሰሌዳ እንዲዘጋጅ ማድረግ፣ ማጽደቅ እንደአስፈላጊነቱ ማሻሻልና መፈጸሙን መከታተል፤
23. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ማቅረብ፤
24. በዚህ ህግና በሌሎች ህጎች የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ ማንኛውንም ተግባራትን ማከናወን፡፡