የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓለቲካ ፖርቲዎችን የውስጥ አለመግባባት አፈታት ሥርዓታቸውን ለማጎልበት የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ጀመረ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓለቲካ ፖርቲዎች የውስጥ አለመግባባት አፈታት ስርዓታቸውን አጠናክረው እንዲተገብሩ የሚስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
መልካም አስተዳደርን ለማጎልበት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል የፓለቲካ ፓርቲዎችን አቅም ማጎልበት ይገኝበታል፡፡ የስልጠናው ዋንኛ ዓላማ ፖለቲካ ፓርቲዎች የውስጥ አለመግባባቶችን የሚፈቱበት ዘላቂነት ያለው ጠንካራ አደረጃጀት እና ሥርዓት ፈጥረው አለመግባባቶችን በውስጥ አቅማቸው ለመፍታት እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ፓለቲካ ፓርቲዎች የውስጥ አለመግባባታቸውን በዲሞክራሲያዊ አግባብ፣ ህግን ማዕከል አድረገው ሲፈቱ ጠንካራ ተቋም ከመገንባታቸው ባሻገር በአባላት መካከል ተዓማኒነትና ተጠያቂነትን ያሰፍናል፣ ይህም ሊዲሞክራሲ ግንባታ ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ይህ ስልጠና የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም ለማጠናከር ከሚሰሩ በርካታ ስራዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በአንቀጽ 74/1/ኘ መሰረት የመተዳደሪያ ደንባቸው ውስጥ አለመግባባት የሚፈቱበትን ሥርዓታቸውን እንዲያስቀምጡ ይደነግጋል፡፡
ፓለቲካ ፓርቲዎች የውስጥ አለመግባባቶቻቸውን በውስጥ አሠራራቸው መፍታት ሲገባቸው፣ በአባላቶቻቸው መካካል በሚፈጠር ያልተገባ እሰጣ ገባ፤ በመራጩ ህዝብ ላይ በሚፈጠረው አሉታዊ ስሜት እና ገጽታ፤ የሚደግፋቸው መራጭ እምነት የሚሸረሸር ብሎም ደጋፊዎቻቸውን ስለሚያጡ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ አሸንፈው መንግስት የመሆን ትልቅ ሀሳባቸውን ያመክናል፡፡
የፓለቲካ ፓርቲዎች በውስጥ አሰራራቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት አማራጮችን አሟጠው ሳይጠቀሙ፤ ጉዳዮቻቸውን በአብዛኛው ወደ ቦርዱ የመውሰድ አዝማሚያ ይታይባቸዋል ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ ፖለቲካ ፓርቲዎች የውስጣቸውን አለመግባባቶች ሌሎች አካላት እንዲፈቱላቸው ከመሻት ይልቅ በቅድሚያ በራሳቸው አደረጃጀት የውስጥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት መጣር እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሜላትወርቅ ይህ ሥልጠና እውን እንዲሆን የፋይናንስ ድጋፍ ላደረገው የኔዘርላንድ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት እና የካበተ ልምዳቸውን ለማካፈል ፍቃደኛ ለሆኑት አሠልጣኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከሐምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በተሰጠው የመጀመሪያው ዙር የሥልጠና ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር ልምምድ የወሰዳችሁትን ስልጠና መነሻ በማድረግ፣ እየተገበራችሁበት ያለውን የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓታችሁን መፈተሸ እና በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አግባብ ማስተካከል ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ አራት በድምሩ በአምስት ዙሮች ሥልጠናው በተግባር ልምምድ ታግዞ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ ስልጠናው ከክልላዊ እና በሀገራዊ አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ስልሳ ሰድስት የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች የሚሳተፉበት ነው፡፡
