በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የስልክ ቁጥር መረጃ

PDFየፖለቲካ ፓርቲዎች የስልክ ቁጥር መረጃ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ 2015 ዓ.ም. ከቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር

PDFከቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ ላይ ለመወዳደር የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡና ከቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው ፓርቲዎች ዝርዝር

PDFየፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መሰረት ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች እንዲያሟሉ ከተጠየቁት መካከል የሚከተሉት አራት ፓርቲዎች መስፈርቱን ያሟሉ ሲሆን ሁለት ፓርቲዎች ደግሞ ባለሟሟላታቸው መሰረዛቸውን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ መስፈርት በማሟላት ያጠናቀቁ

1. የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/- 39%

2. የአፋር ሕዝብ ፓርቲ /አሕፓ/- 45%

3. የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ጋዴፓ/ - 94%

4. የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ /አነግፓ/ - 48%

ባለሟሟላታቸው የተሰረዙ

1.የመላው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /መኦሕዴፓ/ የመስራች ፊርማ ናሙና ማረጋገጫ ከ35 % በታች በመሆኑ እና የ1,142 መሥራች አባላት የነዋሪነት ማረጋገጫ አይነት ያልተሟላ በመሆኑ፣

2. የሲዳማ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ሲብዴፓ/ - 778 መሥራች አባላት የነዋሪነት ማረጋገጫ አይነት ያልተሟላ በመሆኑ እና በምስክርም መረጋገጡ የቀረበ ነገር ባለመኖሩ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም

NEBE

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በቦርዱ ፓርቲዎች ማሟላት ሚገባቸው ግዴታዎች በሚደነግገው መመሪያ መሰረት ውሳኔዎችን ታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ አድርጓል፡፡  

ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

ታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

 NEBE

 

 

 

የፓለቲካ ፓርቲዎች የእውቅና ምዝገባ ሂደት 

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ እና ለመመዝገብ በሂደት ላይ ያሉ ፓርቲዎች ቁጥር ከ130 በላይ ደርሶ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የአዲሱን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ አዋጅን ተከትሎ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ ህግ የተጠቀሱትን መስፈርቶች አሟልተው እንዲመዘገቡ እንዲሁም በሂደት ላይ ያሉ ፓርቲዎችም መስፈርቶቹን በአዲሱ ህግ እንዲያስተካክሉ በተጨማሪም በአዲሱ ህግ ላይ በተቀመጠው መሠረት ጊዜያዊ ሰርተፍኬት በመውሰድ ለምዝገባቸው እንዲዘጋጁ ድጋፍ ተዘጋጅቷል፡፡   

በቀድሞ ህግ ሠርተፍኬት የነበራቸው እና ምዝገባቸውን በቀድሞ ህግ የጀመሩ ፓርቲዎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ድንጋጌዎች እና አዋጁን ለማስፈጸም ቦርዱ በአዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ባወጣው መመሪያ ቁጥር 3 መሠረት በቀድሞ ህግ ሰርተፍኬት የነበራቸው እና ምዝገባቸውን በቀድሞ ህግ የጀመሩ ፓርቲዎችን ሰነዶች በመመርመር ማሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ አዋጁ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ መመሪያ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደርሳቸው እንዲሁም ማቅረብ የሚገባቸው በደብዳቤ እንዲገለጽላቸው ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት፦

 • አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን (በይፋዊ የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ከ10,000-100,000 ብዛት እንዳላቸው የተረጋገጠ ማህበረሰቦች) ለመወከል ከተቋቋሙ ፓርቲዎች ውጭ የሚገኙት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን የመሥራች አባላት ብዛት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ አሟልተው እንዲያቀርቡ፣ 
 • ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ያላካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጉ በተቀመጠው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ብዛት መሠረት እንዲሁም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች  ለመወከል ከተቋቋሙ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ በተቀመጠው ብዛት መሠረት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ በመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ እንዲያቀርቡ፣ 
 • በ2002 ዓ.ም. እና በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ከመንግሥት የተሰጣቸውን ድጋፍ አስመልክቶ በኦዲተር የተረጋገጠ ወቅታዊ የሂሣብ ሪፖርት እንዲያቀርቡ፣
 • ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂዱበት ጊዜ ያላለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ጉባኤ በማካሄድ በመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ እንዲያቀርቡ ተገልፆላቸዋል፡፡ 

በዚሁ መሠረት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ቀድሞ ሰርተፍኬት ከነበራቸው እና በቀድሞው ህግ ምዝገባ ጀምረው ከነበሩ ከቦርዱ ደብዳቤ ከደረሳቸው 106 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን ያቀረቡ ሲሆን በህጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመሆኑ እየተመረመረ ይገኛል፡፡ ምርመራውም፦

 • ፓርቲዎቹ በደብዳቤ የተገለጸላቸውን ነጥቦች ሁሉንም ማሟላታቸውን ማረጋገጥ (የህገ ደንብ ለውጥ ጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች አቀራረብ፣ የመስራቶች ፊርማ … የመሳሰሉት)፣ 
 • የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን የመሥራች አባላት ብዛት ትክክለኛነትን ለመፈተሽ ካቀረቡት የመሥራች አባላት ዝርዝር ናሙና የማውጣት፣ 
 • ናሙናዎቹ በትክክል ግለሰቦቹ የተፈረሙ መሆናቸውን ወደተፈረሙበት ቦታ በመላክ ማረጋገጥ፣ 
 • የህገ ደንብ ለውጦችና፣ የጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች በትክክል መያያዛቸውን ማረጋገጥን ያጠቃልላል፡፡ 

ይህ እንደተጠናቀቀም ሰነዶቻቸው ካስገቡት 76 ፓርቲዎች መካከል ምን ያህሎቹ መስፈርት እንዳሟሉ በቦርዱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡ 

የጊዜ ማራዘሚያ ጠይቀው አሳማኝ ባለመሆኑ ምክንያት የተሰረዙ ፓርቲዎች 

የሚጠበቅባቸውን ሰነድ ማስገባት ያልቻሉ እና ጊዜ እንዲራዘምላቸው የጠየቁ 16 የፓለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ከስር የተጠቀሱት የ13ቱ አጥጋቢ ምክንያት ባለማቅረባቸው የእውቅና ሰርተፍኬታቸው እንዲሰረዝ ቦርዱ የወሰነ ሲሆን 2ቱ ፓርቲዎች (ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)) እና ወለኔ ሕዝቦች ፓርቲ በፓርቲው የውስጥ ችግር የተነሳ መሆኑ ስለታመነበት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን የኮቪድ ወረርሽን በሚያበቃበት ወቅት አንዲያከናውኑ ቦርዱ ሲወስን ሌሎች ሰነዶቻቸው እየተገመገሙ ይገኛል፡፡ 

የፓርቲዎቹ ዝርዝር፦ 

 1. የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) 
 2. የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) 
 3. የደንጣ ዱባሞ ክችንችላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት  
 4. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ)  
 5. የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ትወብዴድ) 
 6. የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአህድ)  
 7. የኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) 
 8. የመላው አማራ ሕዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) 
 9. የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) 
 10. የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ደቡብ ኮንግረስ) 
 11. የሸኮና አካባቢው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሸአሕዲድ) 
 12. ነጻነትና ሰላም ለኢትዮጵያ ህብረት ፓርቲ (ነጻነትና ሰላም)

 

መስፈርት ለሟሟላት ሰነዶችን ያላቀረቡ ፓርቲዎች ዝርዝር 

ሌሎች 14 ፓርቲዎች ደግሞ ከቦርዱ በተደረገው ጥሪ መሠረት ሰነዶቻቸውን ማቅረብ ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የነዚህ 14 ፓርቲዎች ምዝገባ ሰርተፍኬትም እንዲሰረዝ ቦርዱ ወስኗል፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡ 
የፓርቲዎቹ ዝርዝር፦ 

 1. የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ
 2. መላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
 3. የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ
 4. የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
 5. የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት
 6. የዲል ወቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
 7. የቤንች ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት
 8. የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
 9. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ
 10. የሱማሌ አንድነት ፓርቲ
 11. ነፃነት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ
 12. ብሔራዊ ተሀድሶ ለሰላም ልማት
 13. የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት
 14. የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ

በዚህም መሠረት ቦርዱ ባደረገው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በጠቅላላው 27 ፓርቲዎች ከእውቅና ውጪ አንዲሆኑ የወሰነ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ማጣራት ደግሞ ሰነዶቻቸውን አስገብተው በህጉ መሠረት የእውቅና ሰርተፍኬት ለማግኘት የቻሉት ፓርቲዎች ዝርዝር ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ 

ጊዜያዊ እውቅና ሰርተፍኬት ያገኙ ፓርቲዎች 

ጊዜያዊ የእውቅና ሰርተፍኬት ለ3 ወራት ያህል ፓርቲዎች ለዋና ምዝገባቸው ዝግጅት ያደርጉ ዘንድ የሚሰጥ ጊዜያዊ ሰርተፍኬት ሲሆን አሳማኝ ምክንያት ሲኖር ለተጨማሪ ሶስት ወር ሊራዘም የሚችል ሰርተፍኬት ነው፡፡ ይህ ሰርተፍኬት እንደዋና የፓርቲ ምዝገባ አያገለግልም፡፡ ጊዜያዊ የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተው ለምዝገባ እየተዘጋጁ ያሉት 11 አገር አቀፍ እና 21 ክልላዊ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ 

ማስታወሻ 
የፓርቲዎች ሰነዶች ግምገማ እንደተጠናቀቀ ዝርዝራቸው በዚህ ገጽ ላይ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡ 

በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የፓርቲዎች ምዝገባ መስፈርትን አስመልክቶ የፓርቲዎች ሰነዶች ላይ የተደረገ ምርመራ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 160 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ማንኛውም አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ በአዋጁ የተቀመጡትን መስፈርቶች ቦርዱ በሚያስቀምጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማሟላት ያለበት መሆኑን ይገልጻል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የሚቀመጡትን መስፈርቶች ቦርዱ በሚሰጠው የጊዜ ሰሌዳ ያላሟላ ፓርቲ ቦርዱ ከምዝገባ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድበት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ተመዝግበው የሚገኙ የሀገር አቀፍና ክልል ፓርቲዎች በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. (በአዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረት) ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች እንዲያሟሉ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ 

በቀድሞው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 መሠረት ተመዝግበው ያሉ እና በዚሁ ህግ ለምዝገባ እየተንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና በምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት በመተዳደሪያ ደንባቸው ሊያካትቱ የሚገባቸው ጉዳዮች አዘጋጅቶ ለፓርቲዎች እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን ሁሉም ፓርቲዎች የተገመገሙበት ማጠቃለያ ሰነድ ከስር ይገኛል፡፡ (የራይት ምልክት የተደረገባቸው በመተዳደሪያ ደንባቸው የተሟላ ሲሆን ባዶ የተቀመጠው ያልተሟሉ ናቸው፡፡)

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚገኙ የሀገር አቀፍና ክልል ፓርቲዎች (በአዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረት) ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች የሚያስቀምጠውን መመመርያ ከስር ይገኛል፡፡ 

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚገኙ የሀገር አቀፍና ክልል ፓርቲዎች (በአዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረት) ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች የሚያስቀምጠውን መመመርያ ለማግኘት ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመዝግበው የነበሩ ፓርቲዎች የሰነድ ግምገማ

በክልል ደረጃ ተመዝግበው የነበሩ ፓርቲዎች የሰነድ ግምገማ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚገኙ የሀገር አቀፍና ክልል ፓርቲዎች (በአዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረት)ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች መመርያ