በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሣተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የቀረበ ጥሪ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቋቋሚያ ዐዋጁ ቁጥር 1133/2011 እና በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንዲሁም በመራጮች ትምህርት ዕውቅና አሰጣጥ እና በሥነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር 4/2020 በተደነገገው መሠረት፤ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዲችሉ ዕውቅና የመስጠት ኃላፊነት አለበት።
ቦርዱ በ2018 ዓ.ም. 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በመሆኑም ቦርዱ በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የመራጮች ትምህርት ለመስጠት ፍላጎትና ልምድ ያላቸውንና ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መሥፈርቶች የሚያሟሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዲችሉ ፍቃድ ለመስጠት እንዲያመለክቱ ይጋብዛል።
አመልካቾች ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚጠበቅባቸው ዋና ዋና ዝርዝር መሥፈርቶች:
- በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የተመዘገበና ሕጋዊ የምዝገባ ሠርተፍኬት ያለው መሆን፣
- በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በምርጫና ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ለመሥራት በዓላማው ወይም በሥራ ዝርዝሩ ላይ ያስቀመጠ ወይም ያካተተ፣
- ቦርዱ በሚያስቀምጠው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የአፈጻጸም ሪፖርት ማቅረብ የሚችል፣
- የአካታችነት መርኅን የሚያምንና የሚተገብር፣
- ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ወይም እንቅስቃሴ ነፃ የሆነ፣
- በመራጮች ትምህርት ዕውቅና አሰጣጥ እና ሥነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር 4/2020 ለመራጮች ትምህርት የተቀመጠውን መሥፈርት የሚያሟላ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
የማመልከቻ ሂደቶች፡-
አመልካች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ዝርዝር ሠነዶች:
- በአግባቡ የተሞላና በድርጅቱ የበላይ ኃላፊ የተፈረመ የቦርዱን ማመልከቻ ቅጽ ሞልቶ ማቅረብ፣
- ስለድርጅቱ የሚገልጽ መረጃ (organizational profile) እና የምዝገባ የምስክር ወረቀት ቅጂ፣
- ድርጅቱ በየትኛው ክልል/ቋንቋ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት እንዳቀደ የሚገልጽ መሸኛ ደብዳቤ (cover letter)፣
- ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሥራ ላይ የተገኝ ልምድን የሚገልጽ መረጃ፣
- አመልካች የመራጮች ትምህርት ሊሰጥበት ያቀደው የማስተማሪያ ዘዴና አጠቃላይ የትግበራ ዕቅድ
- ለእያንዳንዱ ክልል ወይም ለእያንዳንዱ የማስተማር እንቅስቃሴ ለመመደብ ያቀደው የበጀት ምንጭና ዝርዝር፣
- የድርጅቱ የቀደመ ተያያዥ ተሣትፎ እንቅስቃሴና ፕሮጀክቶች ቢያንስ ሁለት ሪፈረንስ (reference)፣
- የተፈረመ የማመልከቻ ደብዳቤ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
አመልካቾች ከላይ የተጠቀሱትን ሠነዶች እንደ አንድ ፋይል በማደራጀት በሚከተለው የኢ-ሜል፡ votersedu [at] nebe.org.et () አድራሻ መላክ ይኖርባችኋል።
የማመልከቻ ጊዜ:
ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ይሆናል፡፡ አመልካቾች ሠነዶቻቸውን ከላይ በተጠቀስው ጊዜ ውስጥ ብቻ አፍሪካ ጎዳና ቦሌ. ፊላሚንጎ ሬስቶራንት ገባ ብሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና መሥሪያ ቤት ቢሮ ቁጥር 106 ወይም በኢ-ሜል አድራሻ votersedu [at] nebe.org.et () ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡
የማመልከቻ ቅጹን ለማግኘት ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ