Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚያደርገውን የ6 ኛው ዙር ቀሪና የድጋሚ ምርጫን ለመዘገብ ከቦርዱ እውቅና ላገኙ የመገናኛ ብዙኃን ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ሥልጠና ሠጠ፡፡

ስልጠናው የመገናኛ ብዙኃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ ስነ ምግባርን ላይ አትኩሮት አድርጎ የምርጫ ዑደትና የምርጫ ሕግ ማዕቀፍን፤ ምርጫውን የተመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎችን፤ አካታች የምርጫ ዘገባ ባህሪያትን እና የተዛቡ፤አሳሳች፤አደናጋሪና በአጋጣሚ ወይም ሆን ተብለው የሚፈጠሩ የመረጃ መዛባቶችን እና የመረጃዎችን ትክክለኛነት ለመፈተሽ በሚያስችሉ የዲጂታል እውቀቶች እና አጠቃቀሞች ዙሪያ ያተኮረ ነበር፡፡

በስልጠናው የመገናኛ ብዙኃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ ምግባር እና አሰራር መመሪያ ቁጥር 02/2013 እና የምርጫ አዋጁ (1162/2011) አንቀፅ 126 የሚዘረዝሯቸውን የምርጫን ሂደት ለመከታተል እና ለመዘገብ የተዘረዘሩ የሕግ ማዕቀፎችን ተከትሎ ጋዜጠኛች ሊከተሏቸው በሚገቧቸው የምርጫ ዘገባ ስነ-ምግባር እና ግዴታዎች ዙሪያ ሰፊ መረጃ ተሠቷል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ በሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ሌሎች እኩል ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች ላይ አድሏዊ እና አግላይ አሉታዊ አመለካከትን የሚፈጥሩ ዘገባዎችን በመከላከል ረገድ በሥልጠናው ወቅት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የተዛባ መረጃ፤አሳሳችና አደናጋሪ መረጃዎችን መፈተሸን እና የአንድን መረጃ እውነተኛነት ማረጋገጫ መንገዶችን በተመለከተ በሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሃገር የተፈጠሩ ሁነቶችን በናሙና መልክ በማንሳት ጭምር በሥልጠናው ተሳታፊ ለነበሩት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለማስረዳት ጥረት ተደርጓል፡፡

ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምርጫው በሚከናወንባቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ፤በአፋር፤በሶማሌ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚካሄዱትን የምርጫ ዓይነቶች፤ የተከናወኑ ተግባራትን፤ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እና በቀጣይ ቀናት የሚካሄዱትን የምርጫ ሥራዎች በተመለከተ ገለፃ ተሰቷል፡፡ ምርጫው በአራቱ የምርጫ ክልሎች በሚገኙ በ29 የምርጫ ክልሎች 1258 የምርጫ ጣቢያዎች ከ12 ፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ 380 ዕጩዎች እንደሚሳተፉበትም ተገልጻል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከጋዜጠኞቹ ለተነሱ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የእለቱን ሥልጠና በንግግር የዘጉት የምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል ብዙወርቅ ከተተ ቦርዱ እንዲህ ዓይነት መሰል ሥልጠናዎች ማዘጋጀቱ የቦርዱን የምርጫ ሕጎች እና አሠራሮች ለመገናኛ ብዙኃን በቅርበት ለማስገንዘብ ያለው ሚና እጅግ የላቀ እና ጠቃሚ መሆኑን አውስተው ቦርዱ በቅርቡ ባስተዋወቀው የአምስት ዓመት ስትራቴጂው ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርጋቸው ውይይቶች በብዛት ስለሚኖሩ ይህን መሰል የሥልጠናና የውውይት መድረክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

Share this post