የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛ ዙር የጠቅላላ ምርጫ ባልተከናወነባቸው ክልሎች ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማካሄድ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን በማጠናቀቅ የኦፕሬሽናል ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በዚሁ መሰረት በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ 2 የምርጫ ክልል የድጋሚ ምርጫ የሚከናወን ሲሆን ከዚህ በፊት የመራጮች ምዝገባ የተከናወነባቸው መዝገቦች ምዝገባው ከተከናወነ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ በርጥበት ምክንያት በመበላሸታቸው የመዝገቦቹ አንደኛው ገጽ ከሌላኛው ጋር ተጣብቆ ለመለየት አዳጋች በመሆኑ ምርጫውን ለማከናወን የማያስችሉበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

ቦርዱ ይህንን መነሻ በማድረግ በእነዚህ የመራጮች መዝገብ ምርጫ ማከናወን አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒነት የሚያሳጣ የምርጫ ውጤቱንም የሚያዛባ በመሆኑና በሌላ በኩል የመራጮች ድምፅ ዋጋ ያለው ይሆን ዘንድ መራጮች ተመዝግበው ድምጽ እንዲሰጡ ለማስቻል እና ምርጫውንም ፍትሃዊ፣ ግልጽ እና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ለማስፈጸም በማቀድ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ 2 ምርጫ ክልል የሚካሄደውን የድጋሚ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ አሰጣጥ በተመሳሳይ ቀን እንዲከናወን ወስኗል።

በመሆኑም ቦርዱ በምርጫ ቀን የሚመዘገቡት እና ድምጽ የሚሰጡትን የመራጮች ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት በምርጫ ጣቢያዎች መጨናነቅ እንዳይፈጠር በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሚኖረው የመራጮች ቁጥር ከ 750 የማይበልጥ እንዲሆን የወሰነ ሲሆን በዚሁ መሰረት በምርጫ ክልሉ 71 የነበረው የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር 52 የምርጫ ጣቢያዎች ተጨምረው ወደ 123 ምርጫ ጣቢያዎች ከፍ እንዲል ተደርጓል።

በዚሁ መሰረት ቦርዱ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ቁጥር 2 ምርጫ ክልል የሚያካሂደው የድጋሚ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ አሰጣጥ በተመሳሳይ ቀን ሰኔ 9 ቀን 2016ዓ.ም. የሚያከናውን መሆኑን ያሳውቃል።