Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሥነ-ዜጋ ትምህርት እና በምርጫ ዙሪያ የተዘጋጁ የኅትመት ውጤቶችን በሕዝብ ቤተ-መጻሕፍትና በተለያዩ ተቋማት የማሠራጨት ሥራ አከናወነ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በቦርዱ ማቋቋሚያ ዐዋጅ 1133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር የሥነ-ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት እንደሚሰጥ እና እንደሚያስተባብር ይታወቃል። ይህውም መራጮች በቂ ምርጫ ነክ ግንዛቤ የሚያገኙባቸውን የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ማለትም በኅትመት ውጤቶች (በበራሪ ወረቀቶች፣ በቡክሌት፣ በብሮሸሮች እና በሌሎች አማራጮች) ግንዛቤ የሚፈጥሩ መልዕክቶችን በማዘጋጀት በትምህርት ተቋማት፣ በቤተ-መጻሕፍት እንዲሁም በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ በማስቀመጥ ለዜጎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ ይሠራል። ቦርዱ ከላይ የተጠቀሰውን ኃላፊነት ለመወጣት በቦርዱ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ክፍል አማካኝነት የግንዛቤ መስጫ ኅትመቶቹን በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲሁም በብሬልም ጭምር እያዘጋጀ በማሠራጨት ላይ ይገኛል።

የቦርዱ የሥነ-ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት የሥራ ክፍል በዴሞክራሲና በዴሞክራሲያዊ ሂደት ግንባታ፣ በምርጫ እና ከምርጫ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የኅትመት ውጤቶችን ማለትም “ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች?”፣ ”ምርጫ በኢትዮጵያ”፣ ”ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ”፣ ”ዲሞክራሲ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት”፣ እንዲሁም “የምርጫ ሂደት” በሚል ርዕስ የተዘጋጁ አምስት ዓይነት ብሮሸሮችን በአማርኛ ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በአፋርኛ፣ በሱማሊኛ፣ እንዲሁም በሲዳምኛ ቋንቋ ያዘጋጀ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ‘ምርጫ በኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ ወደ 28 የሚጠጉ በዲሞክራሲ እና በምርጫ ዙርያ የተዘጋጁ መልዕክቶች ያሉባቸው መጽሔቶች (ቡክሌቶች) እንዲካተቱበት ተደርጓል።

የሥራ ክፍሉ ከላይ ከተጠቀሱት የኅትመት ውጤቶች በተጨማሪ ከቦርዱ የስርዓተ ፆታ እና ማህበራዊ አካታችነት እና የውጭ ግንኙነት የሥራ ክፍሎች ጋር በመተባበር በብሬል የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ 1162/2011ን በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም መሰረት ከነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በምርጫ እና ሥነ-ዜጋ ትምህርት ዙሪያ የተዘጋጁትን የኅትመት ውጤቶች በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት 77 ለሚሆኑ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ የቤተ-መጻሕፍት ማዕከላት እና ተቋሞች ተሰራጭቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብዛታቸው 12,700 የሚሆኑ ብሮሸሮች፣ 1,980 መጽሔቶችን (ቡክሌቶችን)፣ እንዲሁም 1,620 የሚሆኑ “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011”ን የማሠራጨት ሥራ ሠርቷል። ይህንን በሁለት ቅጽና በብሬል ጭምር የተዘጋጀውን ዐዋጅ ከሰማንያ በላይ ለሚሆኑ ተቋማት ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ በቀጣይም በሌሎች ተቋማትና በክልሎች የማዳረስ ሥራ የሚሠራ ይሆናል።

Share this post