የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የሚደረገውን የድጋሜ የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የሚደረገውን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ምርጫ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትላንትናው ዕለት ሚያዚያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አካሄደ። የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዩች ቋሚ ኮሚቴ ተወካዩች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የዞኑ አመራሮችና የፀጥታ አካላት እንዲሁም የፌደራል ፖሊስና የፍትሕ ሚኒስቴር ተወካዮች የተገኙበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም የመድረኩ ዋና ዐላማ በወላይታ ዞን የተደረገው ሕዝበ ውሣኔ ላይ ቀደም ሲል ያጋጠሙ የሕግ ጥሠቶች በድጋሚ እንዳይፈጠሩ አስቻይ ሁኔታዎችን በጋራ ለመፍጠር ታሳቢ እንዳደረገና ይህንንም ለማድረግ የመድረኩ ተሣታፊ የሆኑት ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ በማሰብ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።
የምክትል ሰብሳቢውን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የምርጫ ኦፕሬሽን አማካሪ በሆኑት ብሩከ ወንደሰን አማካኝነት የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔውን ዝግጅትና ተፈጻሚ የሚደረግበትን የጊዜ ሠሌዳ አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል። የቦርዱ የሕግ ክፍል ሀላፊ በሆኑት መነን አበበ አማካኝነትም እንዲሁ በወላይታ ዞን ላይ የተሠረዘው የሕዝበ ውሣኔ ላይ ያጋጠሙ የሕግ ጥሠቶችን በተመለከተ በፌደራል ፖሊስና በፍትሕ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራ የክትትል ሥራ ውጤት የሆነ ሪፖርት ማብራሪያ ቀርቧል።
በዚህም መሠረት የሕዝበ ውሣኔ ምርጫው ዋና ዋና ተግባራትን ማለትም፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሂደትና ሥልጠና የሚሠጥበት ጊዜን፣ የምርጫ ጽ/ቤቶች አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩበት ጊዜን፣ የመራጮች ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጫ ጊዜን፣ የምርጫ ቁሳቁስ የግዢ፣ የማሸግና የሥርጭት ጊዜን፣ የጥሞና ጊዜና የምርጫ ቀንን እንዲሁም የተረጋገጠ የሕዝበ ውሣኔ ውጤት በቦርዱ ይፋ የሚሆንበት ቀን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ የቀረበ ሲሆን፤ ዝርዝር ተግባራቱ ተፈጻሚ የሚደረጉበት የጊዜ ሠሌዳም ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚሆንና የሕዝበ ውሣኔው ድምፅ መስጫ ቀንም ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚሆን ተገልጿል።
ቀደም ሲል በወላይታ ዞን ላይ በተካሄደው ሕዝበ ውሣኔ የመራጮች ምዝገባና በምርጫው ቀን ያጋጠሙ የሕግ ጥሠቶችን በተመለከተ ቦርዱ ባረደገው የክትትልና የማጣራት ሥራ ከፍተኛ የሕግ ጥሠት መኖሩን በማመን ጉዳዩ በፌደራለ ፖሊስ ማጣራት እንዲደረግበት ያደረገ መሆኑንና በዚህም እስካሁን ድረስ በፌደራል ፖሊስና በፍትሕ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራ የክትትል ሥራ ውጤትን አስመልክቶ ሪፖርት ቀርቧል። በሪፖርቱም በመራጮች ምዝገባ ወቅት የተፈረሙ የመራጮች ፊርማና በምርጫ ቀን የተፈረሙ ፊርማዎች መለያየት፣ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ዜጎች እንዲመርጡ ማድረግ፣ ያለፊርማ የመራጮች ካርድ የወሰዱ መራጮች መኖር፣ የመራጮች በግንባር ሳይቀርቡ ካርድ መውሰድ፣ ታጭቀው የተከገኙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መገኘታቸው፣ በምርጫው ቀን የማስፈራራትና የምርጫውን ሚሥጥራዊነት የመጣሥ ተግባራት ላይ ፌደራል ፖሊስና ፍትሕ ሚኒስቴር ባደረጉት ማጣራት፤ የድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ በሰጠው መራጭ ቁጥርና ድምፅ ለመስጠት በተመዘገበው መራጭ ቁጥር ከፍተኛ ልዩነት መኖሩንና ቦርዱ ያቀረባቸው የሕግ ጥሠቶቸ በተጨባጭ መኖራቸውን ማረጋገጡን በሪፖርቱ ቀርቧል።
ፌደራል ፖሊስና ፍትሕ ሚኒስቴር ባደረጉት ማጣራት 136 ተጠርጣሪዎቸ እንደተለዩና ከነዚህም ውስጥ 94 ተጠርጣሪዎች እንደተያዙ ተገልጿል። በፎረንሲክ ምርመራ የዐሻራና የፊርማ ማጣራት ምርመራው፣ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን የማፈላለግ ሂደቱም እንዲሁ የቀጠለ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል። የድጋሚ ምርጫ ዝግጅትን፣ የጊዜ ሠሌዳውንና የወንጀል ምርመራ ሂደቱ አሁናዊ ሪፖርት ላይ የቀረበውን ማብራሪያን ተከትሎ ከተሣታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ የመራጮች ምዝገባውንና የምርጫውን ቀን በተመሳሳይ ቀን ማድረጉ የሚወስደው ጊዜ ላይ፣ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ላይ የፍርድ ውሣኔ ሳይሰጥ የድጋሜ ምርጫ የማድረጉን አግባብነት፣ እንዲሁም የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄን የተመከቱት ይጠቀሳሉ።
የድጋሜ ምርጫው የመራጮች ምዝገባና ምርጫው በተመሳሳይ ቀን መደረጋቸው በተመለከተ ለቀረቡት ጥያቄዎች በቦርዱ በኩል ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፣ ይኽውም ቦርዱ ይህን ሲወሥን ሊፈጠሩ የሚችሉ የሕግ ጥሠቶችን ለማስቀረት በማሰብ መሆኑንና ይህንንም በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስፈጸምም ቀደም ሲል የነበሩትን የምርጫ ማስተባበሪያ ማዕከላት ከስምንት ወደ 11 ከፍ እንዳደረገና ተጨማሪ 692 ምርጫ ጣቢያዎችን በመክፈት በአንድ ምርጫ ጣቢያ ይስተናገድ የነበረውን 1,500 የመራጮች ቁጥር ወደ 800 ዝቅ ለማድረግ እንደታሰበ፣ በማስፈጸም የሚሠማሩትን አስፈጻሚዎች ቁጥርም ቀደም ሲል ከነበረው 5,560 ወደ 9,020 ምርጫ አስፈጻሚዎች ከፍ በማድረግ እንደሚከናወን ተብራርቷል። ይህም ሲሆን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከፍተኛ አፈጻጸም ካሳዩ ምርጫ አስፈጻሚዎች ውስጥ የሚመለመሉ 5,412 አስፈጻሚዎችን ከአዲስ አበባ የሚሣተፉ ሲሆን ቀሪ 3,608 ደ’ሞ ከወላይታ የሚሣተፉ እንደሚሆን ተገልጿል።
ወንጀል ፈጻሚዎቹ ላይ የፍርድ ውሣኔ ሳሰጥ የድጋሜ ምርጫ ማድረጉን አግባብነት ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር ተወካይ በሆኑት እዮሲያድ አበጀ ማብራሪያ የተሰጡ ሲሆን፤ 352 መዝገቦች እያንዳንዳቸው ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የፈረሙበት መሆኑን፣ ይህንንም ለማጣራት ማን የትኛው መዝገብ ላይ ፈረመ የሚለውን በፎረንሲክ በማጣራት የፊርማ አለመመሳሰሎችን መለየት ረጅም ጊዜ የሚጠይቅና ውስብስብ የምርመራ ሂደት በመሆኑ በሣምንታትና በወራት ዕድሜ ለመጨረስ የሚቻል አለመሆኑን አብራርተዋል። ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሰል ወንጀሎችን የማጣራት ሂደት የመጀመሪያ ልምዱ መሆኑም ከግንዛቤ ሊገባ የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል። በመጨረሻም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር የድጋሜ ሕዝበ ውሣኔው ላይ የተደረገው የመጀመሪያው መድረክ ማብቂያ ሆኗል።