Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚያካሂደውን ሕዝበ ውሣኔ ለማስፈጸም የተመለመሉ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎችን ለሚያሠለጥኑ የመሥክ አሠልጣኞች ኅዳር 27-29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሥልጠና ሰጠ

በቦርዱ የስልጠና ስራ ክፍል ለ299 የመሥክ አሠልጣኞች በሁለት ዙር የተሰጠው ሥልጠና በአርባ ምንጭ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ ሥልጠናውም በሕዝበ ውሣኔው የመራጮች ምዝገባ ሂደት የተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚከናወኑ ተግባራትና ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችን የተመለከተ የንደፈ ሃሳብና የተግባር ልምምድ አካቷል።

ስለሕዝበ ውሣኔው አደረጃጀት፤ ስለሚኖረው የሥራ ኃላፊነትና ድርሻ፤ የቅድመ ምዝገባ ጊዜ ተግባራት፣ ለመራጮች ምዝገባ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ቁሳቁሶች፣ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶች የሚታሸጉበትና የሚጓጓዙበት ሥርዓት፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ የመራጮች መዝገብ ይፋ የሚደረግበት አግባብ፣ እንዲሁም ሥርዓተ-ፆታ እና አካታችነት በሥልጠናው ትኩረት ከተደረገባቸው ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ሥልጠናውን ወስደው ያጠናቀቁ ሠልጣኞች፤ ወደ ተመደቡባቸው የሥልጠና ማዕከላት በመሄድ የመራጮች ምዝገባ አጠቃላይ ሂደትን በተመለከተ ለምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ሥልጠና የሚሰጡ ይሆናል።

Share this post